ጅማ አባ ጅፋር እና ናና ሰርቪስ በጋራ ሊተገበሯቸው ባሉ ስራዎች ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

የደጋፊዎች ምዝገባ፣ ወርሃዊ መዋጮ፣ ክለቡ ደጋፊዎች ሊያስተላልፍ የሚፈልገውን ማንኛውም መረጃዎች በተመለከተ እንዲሁም የክለቡን የገንዘብ አቅም ለማጠናከር በማሰብ የጅማ አባጅፋር እግርኳስ ክለብ ከናና ሰርቪስ ኃ/የተ/የግል ማኅበር ጋር በጋራ ሊሰሯቸው ባሰቧቸው ስራዎች ዙርያ ዛሬ በማግኖሊያ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጅማ አባጅፋር ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ዳምጠው እና የናና ሰርቪስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ደጉ እንዲሁም የሚዲያ አካላት በተገኙበት በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ አስቀድሞ ንግግር ያደረጉት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ” ጅማ አባጅፋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ስኬታማ ውጤት እያስመዘገበ ያለ ክለብ ነው። ይህ ስኬቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተፈለገ ቡድኑን ዘመኑ የሚጠይቀው ሳይንሳዊ አሰራርን ማስገባት እና የክለቡን የፋይናስ አቅም ለማሳደግ በማሰብ ነው ከናና ሰርቪስ ጋር ተባብሮ አብሮ ለመስራት ተማምነን ወደዚህ የገባነው።” ብለዋል።

በመቀጠል ገለፃ ያደረጉት የናና ሰርቪስ ሥራ አስኪያጅ ከጅማ አባጅፋር ጋር በጋራ ለመስራት ያነሳሳቸው ምክንያት ” አባጅፋር ትልቅ ክለብ ነው። በርካታ ደጋፊዎችም አሉት። እነዚህ እምቅ አቅሞችን ወደ ገንዘብ በመቀየር የክለቡን አቅም በማሳደግ ረገድ የታሰበ ነው።” ሲሉ ገልፀው ሊሰሩ የታሰቡ የስራ እቅዶችን በዝርዝር አቅርበዋል።

* ሁሉም ደጋፊዎች በያሉበት ቦታ በስማርት ስልካቸው በአጭር የፁሁፍ መልክት 6732 help ብለው በነፃ መልክት በመላክ ይመዘገባሉ። በዚህም የክለቡን አገልግሎቶች ይረዳሉ ፣ የገንዘብ እርዳታ እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ ። በአማርኛ ወይም በኦሮሚኛ መልዕክት ለመጠቀም በነፃ lang ብለው ወደ 6732 መላክም ይችላሉ።

* የክለቡን ትኩስ ዜናዎች የውድድር መርሀግብሮች ፣ ውጤቶች በአጠቃላይ ክለቡ ለደጋፊዎቹ ሊያሳውቅ የፈለገውን ማንኛውም መረጃዎች ማስተላለፍ

* ለውጤታማ ተጫዋቾች እውቅና ለመስጠት እና ሌሎች ያልተሳካላቸው ተጫዋቾች ለማነቃቃት የወሩን፣ የሳምንቱን እንዲሁም የዓመቱን ምርጥ ተጫዋቾች ደጋፊዎች በአጭር መልክት በመላክ መምረጥ።

* ደጋፊዎች ለክለቡ መሻሻል አልያም በወቅታዊ አቋሙ ከተደሰቱ ሀሳብ የሚሰጡበት በአንድ የጽሁፍ መልክት 5 ብር የሚገኝበት በ8766 መልዕክት በመላክ ከሚገኘው ገቢ ክለቡን ማገዝ የሚቻልበት ስራ ተዘጋጅቷል።

በመቀጠል ወደፊት በሁለተኛ ምዕራፍ ለመስራት የታሰቡትን ሲያብራሩ

1ኛ. ክለቡ ሊሸጣቸው ሊያሰራጫቸው የሚፈልጋቸውን ማንኛውንም የስፖርት ቁሳቁሶች፣ ፎቶዎች፣ አርማዎች፣ በክለቡ ስም የተሰሩ የፅህፈት መሳሪያዎች ማስታወሻዎች በአጠቃላይ የበይነ መረብ ግብይት (online shopping) መፍጠር

2ኛ. ደጋፊዎችም ሆኑ ማንኛውም ተመልካቾች ካሉበት ቦታ ሆነው የወንበር ቁጥር መርጠው የጨዋታ ትኬት የሚገዙበት ሁኔታ መፍጠር።

3ኛ. ጅማ አባ ጅፈር እግርኳስ ክለብ የሞባይል መተግበሪያ (APP) ይኖረዋል። ይህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ብቻ ሳይሆን ከተለያlዩ የፋይናንስ ተቋሞች ጋር የሚያገናኘው ሲሆን ክለቡ እና ደጋፊው የሚደጋገፉበት ይሆናል።

በማስከተል በዕለቱ ከተገኙት የሚዲያ አካላት ጥየቄዎች ቀርበዋል። መተግበሪያ (APP) የስማርት ስልክ ስልክ ይፈልጋል፤ ብዙ ማኅበረሰብ ደግሞ እየተጠቀመ ባለመሆኑ ክለቡ ለምን የራሱ ዌብሳይት አይኖረም? ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ አቶ አብርሃም ሲመልሱ ” ኢትዮጵያ ውስጥ ከቴሌ ባገኘነው መረጃ ወደ 22 ሚሊዮን ግለሰቦች የስማርት ስልክ ተጠቃሚ ናቸው የሚል መረጃ አለን። ስለዚህ ተደራሽ እንሆናለን የሚል ግምት ስላለን ነው ይሄን ሀሳብ ያመጣነው። ዌብሳይት በተመለከተ ሰርተን ጨርሰናል፤ ሆኖም አንዳንድ የቀሩ ያልተሟሉ ነገሮች በመኖራቸው እንጂ ሰርተን ጨርሰናል።” ብለዋል።

የመቀመጫ ወንበር በሌለው ሜዳ የወንበር ትኬት ለመሸጥ መታሰቡ እና ክለቡ የገንዘብ ችግር እንዳለበት እየተነገረ ባለበት ሰዓት ይህን ማሰብ እንዴት ያዩታል የሚለውን ጥያቄ ደግሞ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ሲመልሱ ” የገንዘብ ችግር ክለቡ የለበትም። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ እግርኳስ አትራፊ አይደለም። ሁሉም ክለቦች የመንግስት ጥገኛ ናቸው። ከመንግስት ዓመታዊ በጀት ሲለቀቅ የራሱ የሆነ አሰራር በመኖሩ ዘገየ እንጂ ክለቡ የገንዘብ ችግር የለበትም። አሁን ሁሉ ነገር ተስተካክሏል። ያም ቢሆን አባጅፋር የራሱን የፋይናስ አቅም ለመገንባት የተለያዩ የአስተዳደር እና አደረጃጀት ሰራ እየሰራ ነው። እንደነዚህ ያሉ ስምምነቶችን የፈፀምነው ከዚህ አኳያ ነው። የስታዲየም የወንበር መቀመጫ የለውም ለተባለው በቀጣይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስቴዲየም የመጠቀም ዕቅድ አለን፤ ከዛ ባሻገር አንድን ነገር ሳንጀምረው ስጋት የምናስቀምጥ ከሆነ ስራ አይሰራም። ወደፊት ብዙ ነገሮችን እያስተካከልን እንሄዳለን። ናና ጋር በምንሰራው በዚህ ፕሮጀክት ምንም አይነት ገንዘብ አላወጣንም። እነርሱ እኛን ለማገዝ በትብብር እየሰሩ ነው። ” ብለዋል።

በመጨረሻም ክለቡ ሚዲያው በአብሮነት እንዲሰራ መልክት በማስተላለፍ የጋዜጣዊ መግለጫው ፍፃሜው ሆኗል።

error: