የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ለወሳኙ ጨዋታ ጥሪ ተደረገለት

በዚህ ዓመት ድሬዳዋ ከተማን ተቀላቅሎ በቅጣት ከሜዳ ከመራቁ በፊት ጥሩ ብቃት ሲያሳይ የነበረው ናሚቢያዊው አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኔ ሀገሩ ቀጣይ ሳምንት በሉሳካ ከዛምቢያ ጋር ማርች 23 (መጋቢት 14) ለምታደርገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአሰልጣኝ ሪካርዶ ማኔቲ ጥሪ የተደረገላቸው 28 ተጫዋቾች ውስጥ ተካቷል።

በምድብ 11 ከጊኒ ቢሳው፣ ሞዛምቢክ እና ዛምቢያ ጋር የተደለደለችው ናሚቢያ ከምድቡ መሪ ጊኒ ቢሳው ጋር በእኩል 8 ነጥብ እና የጎል ልዩነት በሁለተኛ ደረጃ ስትገኝ ከተከታይዋ ሞዛምቢክ በአንድ ነጥብ ከፍ ብላ ተቀምጣለች። ብርቱ ፉክክር ሲታይበት የነበረው ይህ ምድብ በመጨረሻው ጨዋታ ከዛምቢያ ውጭ ሶስቱም ሃገራት የማለፍ ዕድል ይዘው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ናሚቢያ ከሜዳዋ ውጪ የምታደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲያሳልፋት የትኛውንም ውጤት አስመዝግባ ጊኒ ቢሳው ሞዛምፒክን ካሸነፈችም የኢታሙና ኬይሙኔ ሀገር ለ3ኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የምታመራ ይሆናል።

የ24 ዓመት አጥቂ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከተደረጉ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ጥሪ ተደርጎለት በአንዱ በመጀመርያ ተሰላፊነት ሲጀምር በሁለቱ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል።

ባለፈው ክረምት አሳዳጊ ቡድኑን ቱራ ማጂክን ለቆ ድሬዳዋ ከተማ የተቀላቀለው ይህ የአጥቂ ክፍል ተጫዋች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተጣለበት ቅጣት በመጨረሱ በሁለተኛው ዙር ድሬዳዋ ከተማን የሚያገለግል ይሆናል።

ከአፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ዜና የመቐለ 70 እንደርታው ግብ ጠባቂ ፍሊፔ ኦቮኖም ሀገሩን በአምበልነት እየመራ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን ከሱዳን ጋር ለሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታም ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *