የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ተጠቋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የሁለቱም ምድቦች ሲጠናቀቁ አዳማ እና ሀዋሳ የምድባቸው መሪ በመሆን ጨርሰዋል፡፡

ጠንካራ እና እልህ አስጨራሽ ፉክክርን ከድንቅ ተጫዋቾች ጋር በማዋሀድ እጅግ አስደናቂ ጨዋታን ያስመለከተን የሀዋሳ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በባለሜዳው ሀዋሳ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ 3-2 አሸናፊነት ተፈፅሟል፡፡ ትላንት (ዕሁድ) በርከት ካሉ ተመልካቾች ጋር ታጅቦ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ፍሰትን የተመለከትን ሲሆን ሀዋሳዎች በአጥቂዎቻቸው ጥረት ተደጋጋሚ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ሲችሉ ፈረሰኞቹ በአንፃሩ በመስመር ላይ አስፈሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡

ገና በ4ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ምንተስኖት እንድሪያስ በግራ በኩል የጊዮርጊስን ተከላካይ ክፍል ስህተት ተመልክቶ የሰጠውን ኳስ አማካዩ በዛብህ ካቲቦ በድንቅ አጨራረስ በዛብህ ወደ ግብነት በመለወጥ ሀይቆቹን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ግቧ ስትቆጠር ረዳት ዳኛው አልገባችም በማለት የመልስ ምት ቢያሳይም ከዋናው ዳኛው ጋር ከተነጋገሩ በኃላ ግን ግቧን አፅድቀዋታል ፡፡ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመስመር እንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም እንኳን የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ለመግባት ባይችሉም በታዲዮስ አዱኛ እና ሉክ ፓውሊንሆ አማካኝነት ተደጋጋሚ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በ18ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ዳግማዊ አርዓያ ወደ ውስጥ ገብቶ አክርሮ መትቶ አላዛር ማርቆስ የመለሰበት ፈረሰኞቹን አቻ ለመሆን የተቃረቡበት ነበር ፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽም በሀዋሳ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

በሁለተኛው አጋማሽ እንግዳው ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ መልኩ የተለየ የጨዋታ ቅርፅ ይዞ ወደ ሜዳ ሲገባ ሀዋሳ ከተማዎች በቅርቡ ወደ ዋናው ቡድን ባደገው መስፍን ታፈሰ ልዩነት ፈጣሪ መሆን በመጨረሻም ጣፋጭ ሙሉ ነጥብን ይዘው መውጣት እንዲችሉ አድርጎቸዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ፋታ የለሽ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ታዲዮስ አዱኛ በ50ኛው ደቂቃ ከዳግማዊ አርአያ ያገኘውን ኳስ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ስህተት ታክሎት ግብ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን አቻ አድርጎል። ጨዋታው መሪ ሆኖ ዙሩን ለማጠናቀቅ የሚረዳ በመሆኑ አንፃር የእለቱ ዳኞች በተደጋጋሚ ሲሰሩት የነበረው ስህተት ጨዋታውን ያቀዘቀዘ እና ከተመልካች እና ከሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ተቃውሞ እንዲስተናገድ መንስኤ የሆነ ነበር፡፡

60ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ዳግም መሪ መሆን ችለዋል። ልማደኛው መስፍን ታፈሰ ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ታምራት ንጉሴ በረጅሙ የላከለትን ኳስ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮ ዳግም ወደ 2-1 መሪነት ሀዋሳን አሳድጓል፡፡ ሆኖም ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ የነበረው የሀዋሳው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ስህተት አሁንም ታክሎበት አቡበከር ሙራድ ከአጋማሹ በረጅሙ የላካትን ኳስ ሉክ ፓውሊንሆ በግንባሩ ገጭቶ ፈረሰኞቹን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ጨዋታው በዚሁ ሂደት ተጠናቀቀ ሲባል 88ኛው ደቂቃ  በቀኝ በኩል ሶስት ተከለካዮችን በማለፍ መስፍን ታፈሰ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው  ተመስገን በቀለ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ሀዋሳን አሸናፊ በማድረግ ጨዋታው 3-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በዚህ ጨዋታ ላይ በዳኝነት ረገድ የተመለከትነው ተደጋጋሚ አወዛጋቢ ውሳኔዎች ሊታረሙ የሚገቡ በመሆናቸው ፌዴሬሽኑ እርምቶችን መውሰድ እንዳለት ለመግለፅ እንወዳለን።

ካለፈው ሳምንት ከተደረጉ ሌሎች ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል ሀዋሳ ከተማ አምቦ ጎልን 4-2፤ ድሬዳዋ ከተማ ወላይታ ድቻን 2-1፤ ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 1-0፤ አዲስ አበባ ከተማ ሀላባ ከተማን 2-1፣ ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡናን 3-0 ያሸነፉበት ይጠቀሳሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *