ሁለት ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመዳኘት የሚሰጠው ስልጠና ላይ ተካተዋል

ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ እና ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚመሩ ዳኞችን ለመምረጥ በሞሮኮ ለሚካሄደው ፈተና እና ስልጠና ከተመረጡ 56 ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ተከተዋል።

ከሚያዚያ 20-27 በሞሮኮ መዲና ራባት በሚካሄደው በዚህ ስልጠና ላይ ከ33 ሀገራት የተውጣጡ 56 ዳኞች የተመረጡ ሲሆን ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የሚመረጡ ይሆናል።

ኢትዮጵያዊያኖቹን ጨምሮ የተመረጡት 27 ዋና እና 29 ረዳት ዳኞች በራባት በሚኖራቸው የስምንት ቀናት ቆይታ የህክምና ምርመራ እና የአካል ብቃት ፈተና የሚደረግላቸው ሲሆን በካፍ ኢንስትራክተሮች አማካኝነት የተግባር እና የክፍል ውስጥ ስልጠና ይሰጣቸዋል። በአፍሪካ ዋንጫው ወቅት የሚተገበሩ አዳዲስ የጨዋታ ህጎችም የስልጠናው አካል ናቸው።

በዓምላክ ተሰማ በተደጋጋሚ ትልልቅ ግምት የሚሰጣቸው አህጉራዊ ውድድሮች እየዳኘ የሚገኝ ሲሆን ተመስገን ሳሙኤልም በብሔራዊ ቡድን ማጣርያዎች እና የክለብ ውድድሮች ላይ መዳኘት ችሏል። ይህን ተከትሎም በሰኔ ወር የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከሚዳኙ ዳኞች የመጨረሻ ዝርዝር ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡