“የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የመጨረሻ ቀን ውሎ

የስፖርት ጨዋነት ምንጮች በሚል መሪ ቃል በሼራተን ሆቴል የተለያዩ የስፖርቱ ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሲካሄድ የቆየው የምክክር ጉባዔ በትናትናው ዕለት የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።

የጉባዔው መሪ ባወጡት መርሐግብር መሠረት የተመልካቾች ፀጥታና ደህንነት በተሰኘው ርዕስ የተለያዩ አካለት የጥናት ሀሳባቸውን አቅርበዋል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪ ኮማንደር ወልዳይ እና የአአ ፖሊስ ኮሚሽነር ተወካይ ም/ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በስታዲየም አካባቢ የሚከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስዔዎቻቸውን በዝርዝር አስቀምጠዋል። በዋናነት፡-

– የትኬት አሻሻጥ ስርዓቱ ከጨዋታው ቀን አስቀድሞ አለመሆን ተከትሎ በሚፈጠሩ ግርግሮች የሚነሱ ሁከቶች

– በስታዲየም አካባቢ ዙርያ የሚገኙ መዝናኛ ቤቶች ደጋፊዎች ከልክ በላይ ጠጥተው ወደ ሜዳ መግባት

– የስታዲየሙ አሰራር ለሁከት መንስዔ በመሆኑ በቀላሉ ፍርስራሽ ድንጋዮችን ወንበሮችን በማግኘት የሚፈጠሩ ችግሮች

– ከእግርኳሱ ህግ ፣ ደንብ ውጭ በስታዲየም ውስጥ ደጋፊዎች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ይዘው ሲገኙ ፌዴሬሽኑ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉ ወደ ሌሎች የመዛመት ጉዳይ

– ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን ለይተው አለማወቅ እና ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት አለማስተማር እንዲሁም አጥፍተው ሲገኙ እርምጃ አለመውሰድ

– ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የቡድን መሪዎች ደጋፊን ሊያነሳሱ የሚችሉ ድርጊቶችን መፈፀም

– ግጭቶች እንዲባባሱ የሚያደርጉ ሁሉም ሳይሆን አንዳንድ ሚዲያዎች መኖራቸው

– የፀጥታ አካላት ገለልተኛ የመሆን ችግር ፣ ያልተመጣጠነ እርምጃ መውሰድ ፣ ቸልተኛ መሆን እና የእግርኳስ ሜዳ ላይ ፀጥታውን የምንመራበት ክህሎት አለመኖር ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስኤዎች ናቸው በማለት በዝርዝር አስቀምጠዋል።

በመቀጠል ከቤቱ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን የቀረበው በአዲስ አበባ የሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ብቻ የሚያተኩር በመሆኑ እና አጠቃላይ እንደ ሀገር ያሉትን የፀጥታ ችግሮችን ያልዳሰሰ ስለሆነ በቀጣይ በክልል የሚገኙ የፀጥታ አካላት የሚገኙበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ በመጠቆም ወደ ቀጣይ ጥናታዊ ሀሳብ አቅራቢ አምርቷል።

የስፖርት ሕግና የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖች ደንቦች በሚል ርዕስ የተለያዩ አካላት ጥናታቸውን አቅርበዋል።

አቶ ሚሊዮን ዓለሙ የስፖርት ሕግ በኢትዮጵያ አወቃቀሩ የመንግስት አደረጃጀት እና የህዝብ አደረጃጀት በመባል ለሁለት እንደሚከፈሉ እና አብዛኛዎቹ የሚመሩት በመንግስት ደንቦች ፣ አመራሮች ፣ ውሳኔ ሰጪነት እና የገንዘብ ድካፍ የሚከናወን እነደሆነ አብራርተዋል።

አቶ ሐብታሙ ሲሳይ የመንግስት የስፖርት ተቋማት ግንኙነት እስከምን ድረስ በሚል ፁሁፋቸው ይህን ለመናገር የሚያስችል የተቀመጠ ማዕቀፍ እንደሌለ እና በሌለ ነገር ላይ እያወራን መሆኑን ገልፀው በፖሊስ ፣ በመከላካያ ፣ በከተማ አስተዳደር ፣ በማህበር በተለያየ አደረጃጀት ነው ክለቦች እየተመሩ የሚገኙት ይህ ደግሞ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ተፅእኖ ፈጥሯል። አንድ ክለብ ክለብ ለመሆን ምን ምን ነገሮችን ሟሞላት አለበት የሚለው ነገር በግልፅ መቀመጥ ይገባዋል። የሚመሩበት ወጥ የሆነ ህግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

አቶ ተፈራ ደንበል የኢትዮጵያ እግርኳስ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለጉባኤተኛው በዝርዝር አስረድተው ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የጨዋታ ታዛቢዎች በሚገባ ግልፅ የሆኑ ሪፖርቶችን አለማቅረባቸው ለውሳኔ እንደተቸገሩ ገልፀው የውሳኔ መስጫ ደንቡን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻያ እንደተደረጉበት እና ውሳኔዎች ሌሎች ክለቦች አስተማሪ እንዲሆን ለሚዲያ በፍጥነት ማሳወቅ ጀምረው እንደነበር፤ አሁን የቆመ ነገር በመሆኑ ከፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ተነጋግረው እንደሚስተካከል ገልፀዋል።

ብዙ የጉባዔ ተሳታፊዎችን ስሜት መግዛት የቻለው የትምህርት ቤትና የዩኒቨርስቲ ስፖርት ውድድሮችን አስመልክቶ ዶ/ር ዘሩ በቀለ ግልፅ ችግሮችን አስቀምጠዋል። ዶ/ር ዘሩ የትምህርት ቤቶች ውድድር ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የነበረውን ጠቀሜታ በዝርዝር ካስቀመጡ በኃላ ከ20 ዓመት ወዲህ ያለው የትምህርት ቤቶች ውድድር የሀገሪቱን ዕምቅ አቅም የገደለ ዓመት ነው ብለውታል። የትምህርት አደረጃጀቱ ስፖርትን ፣ ስነ ምግባርን የዘነጋ በመሆኑ ያልሰራነውን ነገር እየጠበቅን የምንገኘው ፣ ትምህርት ቤቶችን ገድለናቸዋል ብለዋል። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በስብሰባዎች የትምህርት ፖሊሲው ይስተካከል ሲባል ይስቁ ነበር። አሁን ላይ እየተፈጠረ ያለው ትውልድ በስፖርት በሥነ ምግባር ያልታነፀ በመሆኑ ችግሩ ገፍቶ መጥቷል። ስለዚህ ውጤታማ ወደነበረው በአንድ ትምህርት ቤት ለስፖርት ትምህርት በቂ ጊዜ እንዲሰጥ መደረግ። የውስጥ (የክፍል) ውድድሮችን እያደረጉ ከእዛ እያለ ክፍለ/ ከተማ ፣ ወረዳ እያለ ሀገር አቀፍ ውድድሮች መደረግ አለባቸው ብለዋል። ይህ በግለሰቦች ይሁንታ ሳይሆን በህግ በደንብ መቀመጥ እንዳለበት ገልፀዋል።

የስፖርት አካዳሚ የልምምድ ስፍራዎች ሥነ ምግባርን አስመልክቶ አቶ አንበሳው እንየው ገለፃ አድርገዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርት አካዳሚዎች አመሰራረት እና አደረጃጀትን ካብራሩ በኃላ በአካዳሚው የሚገኙ ሰልጣኞች የሥነ ምግባር ትምህርት በሚገባ እንደሚሰጥ ገልፀው በአካዳሚ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሲገልፁ የሰልጣኞች አመላመል በዘር ( በሀገር ልጅ) የመሆን ነገር ይታያል፣ ከአካዳሚው ከወጡ በኃላ የሚኖረው የስነ ምግባር ትምህርትም ሆ የስልጠና ጊዜው ማጠር ተጫዋቾችን ወደ አላስፈላጊ ነገር እንዲያመሩ እያደረገ ነው። እንዲሁም ክለቦች በአካዳሚው ሰልጥነው የሚወጡ ልጆችን አለመውሰድ ሌላው ችግር መሆኑን ገልፀዋል።

ከምሳ በኃላ በቀጠለው የከሰዓት ውሎ የስፖርት ሚዲያ አስመልክቶ ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል። የሚዲያውን አጀማመር እና እድገት በማብራራት በጀመረው የጥናት ሀሳቡ የሰፖርታዊ ጨዋነት በየሜዳዎቹ መጓደል መንስኤ እየሆኑ ያሉት መንግስት ለስፖርት ዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ፣ የህግ የበላይነት አለመከበር ፣ ፌዴሬሽኑ ወደ ዘመናዊ አሰራር ለመግባት ፣ የደጋፊዎች ስርአት አልበኝነት ፣ ተወዳዳሪ አካላት እና ሚዲያው ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ናቸው።

” ሚዲያውን በተመለከተ አንዳንድ ጊዜ ስብሰባ ላማሳመር ተብሎ ሁሉንም በጥቅል የመፈረጅ ችግሮች አሉ አጥፊ አካል ካለ በስም ለይቶ ማስረጃ ይዞ መጠየቅ እየተቻለ “ሚዲያዎች ” በሚል ሁሉን ጠቅሎ መውቀስ ተገቢ አይደለም። ሆኖም እንደ ሚዲያ ያሉብንን ችግሮች ላንሳ የአቅም የዕውቀት ክፍተት የተነሳ ለፀብ የሚጋብዙ ስህተት ይሰራሉ ፣ ሙያውን ካለማወቅ የተረጋገጠ መረጃ ሳይያዙ ለአየር ማብቃት ፣ መርህን አለመከተል ከአሰልጣኝ ከተጫዋች ጋር ቅጥ ያጣ ግኑኝነት ፣ ከሙያው ውጭ የማይረቡ ወጣ ያሉ ስራዎች ውስጥ መገኘት እና ባልተገባ መንገድ የተዛባ መረጃ እንዲዘገብ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ክለቦችን በሚያቀርቡትን ጥቅም ተቀይሮ የተሳሰተ ዘገባ የሚያስተላልፍ መኖር ናቸው። ”

በጋዜጠኛ ሃና ገብረሥላሴ” ሴቶች እና ስፖርት በኢትዮጵያ፣ “ጋዜጠኛ ደረጄ ጠገናው ” የስፖርት ስነ ምግባር መጓደል” በሚል ጥናታዊ ሀሳባቸውን በማቅረብ የቀጠለው ጉባዔው ሙስና በስፖርት ዓለም ውስጥ በሚል በሳሙኤል ስለሺ አማካኝነት ሰፊ የሆነ ጥናታዊ ፁሑፍ ቀርቧል። ሙስና ከሚለው የቃል ትርጉም በመነሳት ይቀጥሉና የስፖርት ሙስና አራት ምንጮች አሏቸው እነርሱም በስፖርቱ ያሉ ማህበረሰብ ብዛት ይዞት የመጣው የገንዘብ ምንጭ ፣ የፖለቲካ ተፅእኖ ፣ የንግድ ተፅእኖ (አቋማሪ ድርጅቶች) እና የሜዲካል (ዶፒንግ) መጎልበት ናቸው። የእግር ኳስ ሙስና ምንድን ናቸው? አንደኛ ጨዋታን መሸጥ ( ያልተገባን ውጤት ፍለጋ ጨዋታውን ከሚመሩ ፣ ከሚሳተፉ አካላት ጋር ያልተገባ ግኑኝነት ማድረግ። ሁለተኛ ዝውውርን ማወክ ( ተጫዋች የማይገባውን ደሞዝ እንዲያገኝ አመራሮች አላስፈላጊ ወጪ እንዲያወጡ ማድረግ) ሦስተኛው አስተዳደራዊ ኢ-ፍትሃዊነትነት (ከአመራርነት ምርጫ ጀምሮ እስከ ታችኛው ፅህፈት ቤት ማስመደብ እና የቅጣት ውሳኔዎችን ማስቀየር ያልተገባ የፕሮግራም ለውጥ ማድረግ) አራተኛ በተጫዋች በአሰልጣኝ ቅጥር ፣ ሲባረሩ በቡድን የሚሰሩ ሙስና ናቸው።

ሰፊ ዝርዝር ጥናታቸውን የቀጠሉት አቶ ሳሙኤል መፍትሔ ብለው ሲያስምጡ ጋዜጠኞች የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲሰሩ ከለላ መስጠት ፣ ፌዴሬሽኑ ከፀረ ሙስና ጋር አብሮ መስራት፣ መንግስት ከህዝብ ጉሮሮ ላይ ነጥቆ የሚያቋቁማቸውን ክለቦች ዞር ብሎ መፈተሽ አለበት ብለዋል።

ከተጨማሪ የሻይ እረፍት መልስ ዘጠኝ አንቀፅ ያለው የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባዔው ከመጠናቀቁ አስቀድሞ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የመዝግያ ንግግር አድርገው የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: