ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ወደ ላይ መውጣቱን ቀጥሏል

ከ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን ያስተናገደበት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ጅማ አባጅፋር በ21ኛ ሳምንት ደደቢትን ከረታው ስብስብ ውስጥ ሶስት ለውጦችን በማድረግ በግል ጉዳይ ወደ ኔዘርላንድ ያቀናው ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄን በዘርይሁን ታደለ፣ አክሊሉ ዋለልኝን በአስቻለው ግርማ እንዲሁም ዋለልኝ ገብሬን በመስዑድ መሐመድ ተክተው በ4-4-2 አሰላለፍ ለጨዋታው ሲቀርቡ በተመሳሳይ ሲዳማ ቡናዎች ስሑል ሽረን ከረታው ስብስብ ውስጥ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ዮናታን ፍሰሀን በግሩም አሰፍ፣ ሚሊዮን ሰለሞንን በተስፉ ኤልያስ፣ ሚካኤል ሀሲሳን በዮሴፍ ዩሐንስ በመለወጥ በ4-3-3 አሰላለፍ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ ናረዳቶቻቸው በብቃት መርተው የጨረሱት ጨዋታ የተጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት በታጣቂዎች ጥቃት ህይወቱ ላለፈው የዋልታ ፖሊስ ተጫዋቾች አማኑኤል ብርሃኑ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር። ቀዝቃዛ እና ሳቢ ባልነበረው በመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም መሐል ሜዳ ላይ ከማንሸራሸር ባለፈ ወደ ፊት በመሄድ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ደካማ ነበሩ። ይህን ተከትሎም በረጅሙ ለአዲስ ግደይ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ ቢሞክሩም በጅማ ተከላካዮች እየተጨናገፉ ፍሬ ማፍራት አልቻሉም በአንፃሩ በመከላከሉ ረገድ አባጅፋሮች በሁለቱ መስመሮች የሚያደርጓቸውን የማጥቃት እቅስቃሴ በመገደብ ውጤታማ ነበሩ። ሆኖም ጅማዎችም በተመሳሳይ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም የሚደርጓቸው ሙከራዎች በሲዳማ ቡና ተከላዮች እየተመለሱ ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

በ26ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ ወደ ሲዳማ ግብ ክልል በረጅሙ ለኦኪኪ የተሻገረውን ኳስ ለመቆጣጠር በሚደረግ ጥረት ኦኪኪ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ጅማዎች በተቸገሩበት ሰዓት ወርቃማ ዕድል ቢያገኙም የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ኦኪኪ መትቶት ወደ ውጭ ሰዶታል። በመጀመሪያው አጋማሽ በ41ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ገዛኽኝ ከርቀት ሞክሮ በዘርይሁን በቀላሉ ከተያዘው ሙከራ ውጭም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል የጠራ የጎል ሙከራ ሳይታይ ነበር የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀው፡፡

ከእረፍት መልስ የመጀርያዎቹን አስር ደቂቃዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ተጭነው የተጫወቱት ጅማዎች በተደጋጋሚ ከዲዲዬ ለብሪ እና አስቻለው ግርማ ከሚነሱ ኳሶች እድሎችን በመፍጠር ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ በዚሁ ሂደት የተገኘውን አጋጣሚ በ47ኛው ደቂቃ ተጠቅመውበታል። ከማዕዘን ምት አስቻለው ያሻማው ኳስ በቀጥታ የግቡን ቋሚ ለትሞ ስትመለስ በቅርብ የነበሩት የሲዳማ ተከላካዮች ከግብ ክልሉ ማራቅ ባለመቻላቸው ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የጅማዎች ጫና ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ኳስን ለሲዳማ ቡናዎች በመተው እና ከኳስ ጀርባ በመሆን በረጅሙ ለአጥቂዎች በሚላኩ ኳሶች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረዋል። ሲዳማዎችም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደጠራ የግብ እድል መቀየር ላይ ሲቸገሩ ተስተውለዋል። አዲስ ግደይ በግል ጥረት የሚያደርገው የማጥቃት እንቅስቃሴ በጅማ ተከላካዮች ሲታፈን ሐብታሙ ገዛኸን አልፎ አልፎ ከርቀት ከሚሞክራቸው አጋጣሚዎች ውጤታማ አልነበሩም። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በጅማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጅማ አባ ጅፋሮች በሁለተኛው ዙር ያሳዩትን መነቃቃት በማስቀጠል ነጥባቸውን 37 አድርሰው መሪው መቐለ 70 እንደርታን በርቀት መመልከት ሲጀምሩ በተከታታይ በሜዳቸው ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውንም ቀጥለውበታል፡፡ ሲዳማ ቡና ደግሞ ሽንፈቱን ተከትሎ 37 ነጥቦች ላይ በመርጋት ከመሪው መቐለ ጋር የነበረውን ልዩነት የማጥበብ እድሉን አምክኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: