ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ መቐለን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሻለ

የሊጉን መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ያስተነገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአስቻለው ታመነ የመጨረሻ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰላ ላይ ከሀዋሳ ጋር ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሄኖክ አዱኛ ፣ ታደለ መንገሻ እና አሜ መሀመድን በአስቻለው ታመነ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና አቤል ያለው በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። አዳማን ካሸነፈበት ጨዋታ በተከላካይ እና አማካይ ክፍሉ ላይ ሁለት ቅያሪዎችን ያደረገው መቐለ 70 እንደረታ ደግሞ አሚኑ ነስሩ እና ዮናስ ገረመውን በማሳረፍ ለአንዶህ ኩዌኩ እና ጂብሪል አህመድ የመሰለፍ ዕድልን ሰጥቷል።

በዋልታ ፖሊስ ትግራይ የእግር ኳስ ክለብ ላይ በደረሰው ጥቃት ህይወቱ ላለፈው ተጨዋች አማኑኤል ብርሀነ የህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ተደጋጋሚ የቅጣት እና የማዕዘን ምቶች ተበራክተውበት ቢታይም ሁለቱን ግብ ጠባቂዎች የፈተኑ ጠንካራ ሙከራዎችም አልጠፉትም። ከጅምሩ በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው አጋማሽ የመድረስ ዕቅድ እንደነበራቸው ፍንጭ የሰጡት መቐለዎች 2ኛው ደቂቃ ላይ በፊት አጥቂው ኦሰይ ማውሊ አማካይነት የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በሂደትም በደቂቃዎች ልዩነት በግራ እና በቀኝ ቦታ እየቀየረ ከአማካይ ስፍራ በመነሳት ሲጫወት የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤልን ፍጥነት ለመጠቀም ጥቃቶቻቸውን በሱ ላይ ሲመሰርቱ ይታይ ነበር። 17ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያደረገው ከባድ የቅጣት ምት ሙከራም ከአማኑኤል እንቅስቃሴ በተነሳ የተገኘ ነበር። በአጋማሹ ቡድኑ ባደረገው እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ 35ኛው ደቂቃ ላይ ማወሊ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ኋላ የመለሰለትን ኳስ ሀይደር ሸረፋ በነፃነት ከቅርብ ርቀት አክርሮ ቢሞክርም ፓትሪክ ማታሲ በሚያስደንቅ ቅልጥፍና አድኖበታል። ሆኖም በፍጥነቱ ዝግ ያለው የቡድኑ የቅብብል ሂደት አብዛኛውን የሜዳ ክፍል የሚያቋርጥ አለመሆኑ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር አድርጎታል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሦስቱ አጥቂዎቻቸው የመቐለን ኳስ ምስረታ ከጅምሩ በማፈን ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ሪቻርድ አርተር ስዩም ተስፋዬን በማታለል አክርሮ የመታው ጠንካራ ኳስ ፍልፕ ኦቮኖ ያዳነበትም የባለሜዳዎቹ ቀዳሚ ሙከራ ሆኗል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ለፈጣኑ አጥቂያቸው አቤል ያለው ቀጥተኛ እና ረዘም ያሉ ኳሶች መጣልን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል። ለተለይም 27ኛው ደቂቃ ላይ ለአቤል በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገኝቶ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል አምክኖታል። የባለሜዳዎቹ የመስመር ጥቃት እንደወትሮው ባልነበረበት በዚሁ አጋማሽ መሀል ሜዳ ላይ በሀምፍሬይ ሚዬኖ መሪነት በቅብብሎች ወደ ሳጥን ለመድረስ የሚሞክርበት አግባብም እምብዛም ውጤታማ አልሆነም። በአመዛኙ በቅርብ ርቀት የሚከወኑትን የመቐለዎች ቅብብሎች ግን የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ከመፈጠራቸው እና ኳስ ወደ አደጋ ክልል ከመድረሷ በፊት በመከላከሉ ጊዮርጊሶች የተሻለ ተሳክቶላቸዋል። ቡድኖቹ ያለግብ ተለያይተው ወደ መልበሻ ክፍል በሚያመሩበት ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ስትዋርት ሀል ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ጋር ግብግብ ለመፍጠር የተጋበዙበት ክስተትም ከጨዋታው እንቅስቃሴ በላይ ትኩረትን የሳበ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ለውጦችን ያደረጉት ጊዮርጊሶች በእጅጉ ተሽለው ቀርበዋል። ታደለ መንገሻ አማካይ ክፍሉ ላይ በናትናኤል ቦታ መግባቱ እና ፊት ላይ አቤል ያለው ወደ መስመር ሪቻርድ አርተር ደግሞ ወደ ፊት አጥቂነት መለወጣቸው ብዙ ልዩነትን ፈጥሯል። አቤል በነበረበት የቀኝ መስመር በንፅፅር በተሳኩ ቅብብሎች ደጋግመው ጥቃት የሰነዘሩት ጊዮርጊሶች ተጋጣሚያቸውን ጫና ውስጥ መክተት ችለዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ከአቤል እና አብዱልከሪም ቅብብሎች የተገኘው የአርተር የሳጥን ውስጥ ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ሲወጣ ጨዋታውን ነፍስ በዘራበት ታደለ መንገሻ እንቅስቃሴ ከመቐለ አማካዮች ጀርባ ነፃ ሆኖ በተደጋጋሚ ይታይ የነበረው ሚዮኔም 54ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። 76ኛው ደቂቃ ላይም ከታደለ እግር የተነሳው ሌላ ረጅም ኳስ በበኃይሉ ተሞክሮ በኢቬኖ ልዩ ጥረት ነበር የተመለሰው።

የፈረሰኞቹን ለውጦች መቋቋም ያልቻሉት ምዓም አናብስት የጨዋታ ዕቅዳቸው በማይመስለው መልሶ ማጥቃት ዕድሌችን ለመፍጠር ከመሞከር ባለፈ ኳስ መስርተው መግባት ከብዷቸው ታይቷል። የአማኑኤል እንቅስቃሴም በአስቻለው ታመነ የቅርብ ክትትል የደረግበት የነበረ በመሆኑ ያሬድ ከበደ ወደ ሙከራነት ሳይቀይራቸው ከቀሩ ሁለት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ውጪ ተፅዕኗቸው ወርዶ ታይቷል። ቡድኑ የሚያስቆጭ ዕድል አገኘ ከተባለም በረጅሙ የተሻገረን ኳስ ፓትሪክ ማታሲ በአግባቡ ሳይቆጣረው ቀርቶ ግብ ሊሆንበት በተቃረበበት አጋጣሚ ብቻ ነበር።

ከ75ኛው ደቂቃ በኋላ የተሻለ እርጋታ ታይቶባቸው የነበሩት እንግዶቹ የተፈጠረባቸው ጫና የረገበ ቢመስልም በስተመጨረሻ ግን ግብ አስተናግደዋል። አቤል ያለው ለሪቻርድ አርተር ኳስ ባሻማበት ቅፅበት አንተነህ ገብረክርስቶስ አጥቂውን ተጭኖታል በሚል አሸብር ሰቦቃ 86ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው አስቻለው ታመነም የጨዋታውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል። የአርቢትሩን ውሳኔ የተቃወሙት የመቐለ ተጨዋቾች ኳስ ከመሀል ሊጀመር ሲል በሚከራከሩበት ወቅት ሁኔታውን ለማረጋጋት ወደ ሜዳ የገኑት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከሜዳ ሳይወጡ ጨዋታው መቀጠሉ ሌላኛው የጨዋታው ክስተት ሆኖም አልፏል። በቀሩት ደቂቃዎችም መቐለዎች ወደ ፊት ገፍተው ለመጫወት ቢሞክሩም ጊዮርጊሶች ውጤቱን በማስጠበቅ ማሸነፍ ችለዋል። ባገኙት ድልም ወደ ሦስተኝነት ከፍ በማለት የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስምንት ዝቅ ማድረግ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡