ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

የ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ባህር ዳር ላይ ደቡብ ፖሊስን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ 3-3 አቻ ተለያይቷል።

በአንፃራዊነት ከወትሮ በተለየ ቁጥራቸው ባነሱ ደጋፊዎች ታጅቦ የተከናወነው ጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር ተስተውሎበታል። ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ወደ አዲስ አበባ አቅንተው አስደንጋጭ ሽንፈት ካስተናገዱበት የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አራት ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ሐሪስተን ሄሱ፣ ዳንኤል ኃይሉ፣ ሳላምላክ ተገኝ (በቀይ ካርድ) እና ዜናው ፈረደን በምንተስኖት አሎ፣ ወንድሜነህ ደረጄ፣ ዳግማዊ ሙሉጌታ እና ግርማ ዲሳሳ ቀይረው ለጨዋታው ቀርበዋል። ደቡብ ፖሊሶች ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ከወላይታ ድቻ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሶስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ደስታ ጊቻሞ፣ ዮናስ በርታ እና ብሩክ ኤሊያስን በአዳሙ መሐመድ፣ ብርሃኑ በቀለ እና ላከ ሳኒ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከአራት ቀናት በፊት ህይወቱ ላለፈው የትግራይ ዋልታ ክለብ ተጨዋች አማኑኤል ብርሃኑ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታው በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የባለ ሜዳዎቹ የበላይነት ታይቶበታል። በ5ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በተሻገረ እና ግርማ በሞከረው ሙከራ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ባህር ዳሮች ግብ አስቆጥረው ገና በጊዜ መሪ ለመሆን ሞክረዋል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም ወደ ተጋባዦቹ የግብ ክልል የደረሱት ባህር ዳሮች ግርማ ዲሳሳ ከመዓዘን አሻምቶ አሌክስ አሙዙ በሞከረው የግምባር ኳስ ሌላ ሙከራ አድርገው ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተዳክመው የታዩት ደቡብ ፖሊሶች ምንም አይነት ጥቃት ባህር ዳሮች ላይ ሳይሰነዝሩ ጨዋታቸውን ማድረግ ቀጥለዋል። ከተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያገኙትን ኳስ ወደ ግብ በመምታት ጎል ማስቆጠር የፈለጉት የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ተጨዋቾች በአንፃሩ በ17ኛው እና በ19ኛው ደቂቃ በሞከሩት ሙከራ እጅጉን ወደ ግብ ቀርበው ነበር። በተለይ የሚታወቁበትን የመስመር ላይ ጥቃት በየደቂቃው መሠንዘራቸውን በመቀጠል በ20ኛው ደቂቃ ወሰኑ ከቀኝ መስመር አሻምቶ ፍቃዱ ወርቁ በግምባሩ ባስቆጠረው ግብ መሪ ሆነዋል።

ግብ ካስቆጠሩ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ለሁለተኛ ጎል ወደ ፊት ያመሩት ባህር ዳሮች በግርማ ዲሳሳ አማካኝነት ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ አድርገው ነበር። ከዚህች ደቂቃ በኋላ ግን ጥቃታቸውን በመቀነስ ተረጋግተው ለመጫወት ሞክረዋል። ይህ መረጋጋታቸው የጠቀማቸው ፖሊሶች ከመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በተሻለ ኳስን ከግብ ክልላቸው ጀምሮ በመመስረት ወደ ባህር ዳሮች ግብ ለመድረስ ጥረዋል። በዚህም በ27ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው አክርሮ ከርቀት በመታው ኳስ አቻ ለመሆን ተቃርበዋል። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደ እንቅስቃሴው መልሶ ማጥቃትን ሲከተሉ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በ41ኛው ደቂቃ ያለቀለት እድል አምልጧቸዋል። በዚህ ደቂቃ በፈጣን ሽግግር ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል የደረሱት ፖሊሶች ላኪ ሳኒ ለብርሃኑ በቀለ አቀብሎ ብርሃኑ በሞከረው ሙከራ ነበረ እጅጉን ለጎል የቀረቡ የነበረው። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በባለሜዳዎቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

አምስት ጎሎች የተቆጠሩበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የሜዳ ላይ ፉክክር ታይቶበታል። ገና በ6ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ጎል አስቆጣሪው ፍቃዱ ወርቁ በተራው ለወሰኑ ዓሊ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት ወሰኑ ግብ አስቆጥሯል። መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉት ባህር ዳሮች በ56ኛው ደቂቃ ዳግማዊ ሙሉጌታ በመታው ጥብቅ ኳስ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የነበረባቸውን ክፍተት አሻሽለው የገቡት የገብረክርስቶስ ቢራራ ተጨዋቾች በተለይ በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ጥሩ እድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በዚህም በ57ኛው ደቂቃ ወደ ባህር ዳሮች የግብ ክልል በመድረስ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ወንድሜነህ ደረጄ የተሻ ግዛው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል።

ይህ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የተደናገጡ የሚመስሉት የባህር ዳር የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ስህተቶችን እየሰሩ ራሳቸውን ለግብ ሲያጋልጡ ተስተውሏል። በዚህም በ61ኛው ደቂቃ በሰሩት ስህተት ዘላለም ኢሳይያስ ጎል አስቆጥሮባቸው አቻ ሆነዋል። ፈጣኑን የደቡብ ፖሊስ ጥቃት መቋቋም የተሳናቸው ባህር ዳሮች በሶስት ደቂቃ ልዩነት ሦስተኛ ጎል የተሻ ግዛው አስቆጥሮባቸው መመራት ጀምረዋል።

ከመመራት ወደ መምራት የመጡት ደቡብ ፖሊሶች መሪ ከሆኑ በኋላ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተጫውተዋል። በተቃራኒው ሳይታሰብ የተመሩት ባህር ዳሮች የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች በማስወጣት የአጥቂ ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች በማስገባት በተሻለ ለማጥቃት ሞክረዋል። በዚህም በ70ኛው ደቂቃ ወሰኑ በሞከረው እጅግ አስደንጋጭ ኳስ አቻ ለመሆን ጥረው ግብ ጠባቂው ሐብቴ ከድር እና የግቡ አግዳሚ አውጥቶባቸዋል። ከተገኘ የማሸነፊያ ካልሆነ ደግሞ የአቻነት ጎል ሲፈልጉ የነበሩት ባህር ዳሮች በ78ኛው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት ደረጄ አሻምቶት አሌክስ በሞከረው የግምባር ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። አሁንም ግብ ከማስቆጠር ጥረታቸው ያልቦዘኑት ባህር ዳሮች ተቀይሮ የገባው እንዳለ ደባልቄ በ81ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው የግምባር ኳስ አቻ ሆነዋል።

ሁለት ተጨዋቾችን ብቻ ከፊት በማድረግ ሲከላከሉ የነበሩት ደቡብ ፓሊሶች ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በመልሶ ማጥቃት በመምጣት ጥሩ ሙከራ በብርሃኑ በቀለ አማካኝነት አድርገው መክኖባቸዋል። በሙሉ ሃይላቸው ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በተጨመረው አምስት ደቂቃ ሶስት ጥሩ ጥሩ እድሎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በአንደኛው የጭማሪ ደቂቃ ደረጄ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሐብቴ ሲተፋው ያገኘው ወሰኑ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ አራተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ከወሰኑ በተጨማሪ የአቻነቱን ጎል ያስቆጠረው እንዳለ እንዲሁም የተከላካይ መስመር ተጨዋቹ አሌክስ በሰነዘሯቸው ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረው መክኖባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 3-3 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡