የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 መቐለ ሰባ እንደርታ


ዛሬ 11፡00 ላይ ተጠባቂ በነበረው የሊጉ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መቐለ 70 እንደርታን 1-0 ካሸነፈ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች የሰጧቸው አስተያየቶች እንዲህ ይነበባሉ።

“በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር” ስትዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“ጠንካራ ቡድን ነው የገጠምነው። በመጀመሪያው አጋማሽ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቻቸው ወደራሳቸው ግብ ተጠግተው በመጫወታቸው ከጀርባቸው ለመግባት ተቸግረን ነበር። በዕረፍት ሰዓት ወደ ፊት ገፍተን ለመጫወት እና የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ተነጋግረን ነው የገባነው። ከዛ በተጨማሪም ከፊት የሚና ለውጦችን አድርገናል ፤ ሪቻርድን ወደ ዘጠኝ ቁጥር አቤልን ደግሞ ወደ መስመር አጥቂነት ቀይረናቸዋል። በኃይሉን ደግሞ በሌላኛው ክንፍ አስገብተናል። ያም እንዳሰብነው ሰርቶልናል። ኳስ ስንነጠቅ በከፍተኛ ጫና መልሰን እናገኘው ነበር። ነገር ግን እጅግ በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር።”

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ

“ፍፁም ቅጣት ምቱ ለኛ በዓመቱ የመጀመሪያችን ነው። እነሱ ደግሞ እስካሁን ሰባት ጊዜ አግኝተዋል። አከራካሪ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ያን በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም።”

“የተፈጠረው ስህተት ለሽንፈት ዳርጎናል” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

” ከበድ እና ጠንከር ያለ ጨዋታ ነበር ፤ ለኛም ለነሱም ወሳኝ የነበረ በመሆኑ ማለት ነው። ሁለት ገፅታ ነበረው። በመጀመሪያው አጋማሽ ኳሱን ተቆጣጥረን የመጫወት አቅማችን ጥሩ ነበር። ከእረፍት መልስ ደግሞ እነሱ በተሻለ መልኩ ጫና ፈጥረዋል። መሸነፍ አይገባንም ነበር። የተፈጠረው ስህተት ለሽንፈት ዳርጎናል ማለት ይቻላል። ዳኛው ከአንድም ሁለት ስህተት ነው የፈጠረው። ዳኛ ስለሆነ ውሳኔውን ተቀብለናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡