ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አምስት – ክፍል አንድ)

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics በሶከር ኢትዮጵያ በአማርኛ መቅረብ ከጀመረ 19 ሳምንታትን ተቆጥሯል፡፡ የዛሬው መሠናዶም በሩሲያ እግርኳስ ላይ አተኩሮ ምዕራፍ አምስት መቅረብ ይጀምራል።

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

የተደራጀ/የታቀደበት ትርምስ

በሶቭየት ኅብረት እግርኳስ በወጉ መስፋፋት የጀመረው ዘግየት ብሎ ነው፡፡ ምናልባትም ጨዋታው በታሪክ ውስጥ ጥልቅ ስር ሰደው በሰፊው በተንሰራፉት <ድርጊቶችን በትክክለኛው መንገድ የመከወን> ግትር ሃሳቦች ሳይተበተብ ስርነቀል በሆነ ሁኔታ ፈጥኖ ተቀባይነት ያገኘው ለዚህ ይመስላል፡፡ የብሪታኒያ መርከበኞች በ1860ዎቹ መጀመሪያ በማዕከላዊ ዩክሬይን ከ<ጥቁር ባህር> አቅራቢያ በሚገኙት <ኦዲዜ> የሚባሉ ደቡባዊ የወደብ ከተሞች ውስጥ እግርኳስ ይጫወቱ ጀመር፡፡ <ዘ ሐንተር> የተሰኘው መጽሔት በወቅቱ ጨዋታው ላይ የሚስተዋለውን ግርግርና ከባባድ አካላዊ ጉሽሚያዎች አስመልክቶ ” እግርኳስ ፈርጣማ ጡንቻና ጠንካራ እግሮች ያላቸው ሰዎች የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡ የደካሞቹ እጣ ፈንታማ የዚህ ፍልሚያ ተመልካች መሆን ብቻ ነው፡፡” የሚል ጽሁፍ አውጥቶ ነበር፡፡ ዘጋቢው በአንድ በኩል የእንቅስቃሴውን ሒደት ታቃውሞ፥ በሌላ በኩል ደግሞ ባየው ሁኔታ ግራ ተጋብቶ ስለመጻፉ ማስረጃ አያሻም፡፡

በ1890ዎቹ ጅማሮ የሩሲያ እግርኳስ በአግባቡ የተደራጀ ቅርጽ እየያዘ መጣ፡፡ እንደ ሌሎቹ ቦታዎች ሁሉ በሩሲያም ጨዋታውን በማስተዋወቅ ረገድ ብሪታኒያውያኑ እጅግ የጎላ ድርሻ ነበራቸው፡፡ መጀመሪያ በሴይንት ፒተርስበርግ ቀጥሎ በሞስኮው የሞሮዞቭ ወፍጮ ማሽኖች ማምረቻ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረው ሃሪ ቻርኖክ ሰራተኞቹ ዘወትር ቅዳሜ ቮድካ እየተጎነጩ ከሚዝናኑ ይልቅ ለየት ያለ ተመክሮ እንዲያዳብሩ የማሳመን ዓላማ አንግቦ በቀጣዮቹ ዓመታት ዳይናሞ ሞስኮው የሚል ስያሜ የሚያገኘውን ክለብ አቋቋመ፡፡ የሶቭየቶች ልብ-ወለዳዊ የሥነ ጽሁፍ ፈጠራ የከፍታው ማማ ላይ ሲደርስ እንደታየው በሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገበት የመላው ሩሲያ ቡድኖችን የሚያስተዳድረው የዳይናሞ ስፖርት ክለብ አመራሮች የመለያ ቀለማቸውን ሰማያዊና ነጭ እንዲሆን መረጡ፡፡የከለር ምርጫቸው ለሰው ልጅ በህይወት መቆየት መሰረታዊ ዋስትና የሆኑትን ሁለት ዋነኛ ንጥረ-ነገሮች፥ ማለትም ውሃና አየርን የመወከል ዓላማ እንደበረው መረጃዎች ቢያመለክቱም ምክንያቱ ከዚህ የተለየ ስለመሆኑ የሚያትት ሌላም መላምት ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ “ቻርኖክ የተገኘው ከሰሜን ምዕራባዊቷ የእንግሊዝ ከተማ ብላክበርን ስለሆነ ቡድኑ ዳይናሞ ሞስኮ በሃገሩ ሳለ ይደግፈው የነበረውን የብላክበርን ሮቨርስ መለያ ቀለም እንዲለብስ አደረገ፡፡” የሚለው ለእውነታ የቀረበ ድምዳሜ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

በዚያን ጊዜ ከምዕራባዊ የአህጉሪቱ ክፍል በላቀ የማዕከላዊው አውሮፓ ሃገራት የእግርኳሱ ከባቢ ድባብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ችለዋል፡፡ በ1894 <ሶኮል የስፖርት ክለብ> አጠር ያሉ የትርኢት ውድድሮችን ባዘጋጀበት ጉዞ በአሁን ወቅት የዩክሬናውያን ይዞታ በሆነው ቦታ ላይ <ሌቪቭ> የመጀመሪያውን የእግርኳስ ጨዋታ ስታስተናግድ የኦስትሮ-ሃንጋሪ ግዛት አካል ነበረች፡፡

እንግሊዞች ሩሲያን ከለቀቁ በኋላ በ1936 በሃገሪቷ የብሔራዊ ሊግ ምስረታ ተካሄደ፡፡ (በ1908 <ስፖርት> የተባለ የሩሲያ ቡድን በሴይንት ፒተርስበርግ ከተማ ይካሄድ የነበረውን <የአስፔዳን ዋንጫ> ውድድር ሲያሸንፍ ከሌሎች ሃገራት በመጡ ሰዎች የበላይነት ስር የነበረው የሶቭየት እግርኳስ ቀስበቀስ የኃያልነት መንበሩን ለከተሜው ተወላጆች ማስመለስ ጀመረ፡፡) ይሁን እንጂ የጥንቱ 2-3-5 ፎርሜሽን ተመራጭነት በነበረበት ቀጠለ፡፡ በ1925 ደግሞ ከ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ታክቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መጠነኛ ልዩነቶችን ፈጠረ፡፡ ያኔ ሶቭየት ህብረት ከፊፋ አባልነት በመገለሏ ሃገሪቱ ከሌሎች የውጭ ተጋጣሚዎች ጋር የመጫወት እድሏን ተገደበባት፤ በብዛት አማተር ቡድኖችን የማግኘት ግዴታም ተጋረጠባት፡፡ ያም ሆኖ ሃገሪቱ በእግርኳሱ ረጅም ርቀት ወደኋላ ስለመራመዷ ማንም ከቁብ አልቆጠረውም፤ ድክመቷን የሚያጋልጥ ምልክት ሰጪ ሁኔታም አልተፈጠረም፡፡

በ1937 እነዚያ ሁሉ ተግዳሮቶች በፍጥነት መፍትሄ አገኙ፡፡ በሃገሪቱ የብሄራዊ ሊግ መጀመር እግርኳስ እጅግ በተወሳሰበ ትንታኔ እንዲቃኝ መንገድ ሳይከፍት አልቀረም፡፡ በእግርኳሱ ለታየው ለውጥ መነሳሻ የሆነው አጋጣሚ ግን የቢልባኦ ቡድን ሶቭየት ህብረትን ከረገጠበት ወቅት ይጀምራል፡፡ በስፔን በተካሄደው የእርስበርስ ጦርነት የባስክ ግዛት አቋም ምን እንደሚመስል ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ በመላው ዓለም እንዲደረግ በተወሰነው የጉዞ መርኃግብር ውስጥ እግርኳስ አንዱ ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠሪያ መንገድ ነበር፡፡

በሩሲያ ከውጭ ሃገራት ጋር የሚደረጉ ግጥሚያዎች ብዙም ባለመለመዳቸው አልፎ አልፎ የሚከናወኑት ዓለም አቀፋዊ ጨዋታዎች በታላቅ ጉጉት ይጠበቃሉ፡፡ <ቭራታር (ግብ ጠባቂው)> የተሰኘ የሴሚዮን ቲሜሼንኮ ታዋቂና አስቂኝ ዘፈን በ1937 ከተለቀቀ በኋላ ደግሞ ሃገሪቱ ከሌሎች ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የምታካሂዳቸው የእግርኳስ ፍልሚያዎች ተናፋቂነት ጨመረ፡፡ ከሰራተኛው መደብ በተገኘ አንድ ታታሪ ወጣት ዙሪያ ያጠነጠነውን ሙዚቃዊ ተውኔት ስመጥሩ የትያትር ባለሟል ግሪጎሪ ፕሉዝኒክ በጥሩ ሁኔታ ተጫወተው፡፡ በዚህ ሙዚቃዊ ትዕይንት ወጣቱ የበሰለ ሀባብ ከፍራፍሬ መጫኛ ጋሪ ላይ ወደ መሬት ወድቆ ከመፈጥፈጡ በፊት በፍጥነት ሲይዘው ያሳይ ነበር፡፡ ሶቭየት ህብረት ደግሞ ወደ ሃገሪቱ እየመጡ እግርኳስ ከሚጫወቱ ተጓዥ ቡድኖች ጋር ስትጋጠም በድራማዊ ክስተቶች የታጀበው ሙዚቃ እንዲሰማ ትዕዛዝ አስተላለፈች፡፡ በፊልሙ ላይ ጀግናው ወጣት ተከታታይ የግብ ሙከራዎችን በቀላሉ ካዳነ በኋላ የጨዋታው መገባደጃ ሰዓት ሲቃረብ ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ሮጦ በመሄድ የአሸናፊነት ግብ ሲያስቆጥር የሚያሳይ ትዕይንት አለ፡፡ እንደተጠበቀው የድራማው ማጀቢያ ሙዚቃ ዋነኛ ተልዕኮ ለሃገሬው ህዝብ “ጀግናው በረኛ ራስህን ለፍልሚያ አዘጋጅ፤ የጎሉን አካባቢ የምትቆጣጠረው እኮ አንተ ነህ፤ እናም ከጀርባህ ድንበር ስለመኖሩ አስብ፡፡” የሚለውን ፖለቲካዊ መልዕክት ምሳሌያዊ በሆነ አቀራረብ ማስተላለፍ ነበር፡፡

ከባለ ሰፊ ልምዶቹ ጎብኚዎች መካከል የሚጠቀሱት ባስኮች ግን በሶቭየቶቹ ፕሮፖጋንዳ እምብዛም አልተሸበሩም፤ በቀላሉ የሚበገሩም አልሆኑም፡፡ በ1934ቱ የዓለም ዋንጫ ከተሳተፈው ስብስብ ስድስት ተጫዋቾችን ያካተተ ቡድን ይዘው ወደ ሩሲያ አቀኑ፡፡ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ላይ የWM ፎርሜሽንን ተጠቅመው ሎኮሞቲቭ ሞስኮን 5-1 ድባቅ መቱ፤ ቀጠሉና ዳይናሞዎችን 2-1 ረቱ፡፡ ከዚያም ከሌኒንጋርድ ምርጥ ጋር 2-2 አቻ ከተለያዩ በኋላ ወደ ሞስኮ ተመልሰው ከዳይናሞዎች ማዕከላዊ ቆንጽላ የተመረጡ ምርጦች ላይ ትልቅ ድል ተቀዳጁ፤ በዚህ ጨዋታ ባስካውያኑ በሩሲያውያኑ ላይ የጎል ዶፍ አወረዱባቸውና የ17-4 ውጤት አስመዘገቡ፡፡ በመጨረሻ ጨዋታቸው የሃገሪቱ የሊግ ቻምፒዮን ስፓርታ ሞስኮውን ለመግጠም ተዘጋጁ፡፡ በእንግዳው ቡድን አማካኝነት የተፈጠሩ አሳፋሪ ሽንፈቶችን ለመቀልበስ በቁርጠኝነት የተነሳው የክለቡ አሰልጣኞች ቡድን መሪ ኒኮላይ ስታሮስቲንም ከሌሎች የሃገሪቱ ክለቦች በርካታ ተጫዋቾችን ጠራ፡፡ የዳይናሞ ኪዬቭ አጥቂዎች የነበሩት ቪክቶር ሽሎቭስኪ እና ኮንስታንቲን ሼሆትስኪም የስታሮስቲን ምርጫ ውስጥ ተጠቃለሉ፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በ1935 ፓሪስ ውስጥ በተዘጋጀ ውድድር የኪዬቭ ምርጥ ሬድ ስታር ኦሊምፒክ ላይ የ6-1 ድል ሲያሳካ ወሳኝ ድርሻ ነበራቸው፡፡

ስታሮስቲን በጨዋታው ባስካውያኑን በራሳቸው የአጨዋወት ቅርጽ (Shape-For-Shape) ሊፋለማቸው ወጠነ፡፡ የባስኮቹን የመሃል አጥቂ /Center-Forward/ ኢሶድሮ ላንጋራ ተጽዕኖ እንዲመክት ተብሎ የቡድኑ የመሃል ተከላካይ-አማካይ /Centre-Half/ በሜዳ ላይ የሶስተኛ ተከላካይነት /Third-Back/ ሚና እንዲወስድ አደረገ፡፡ ይሁን እንጂ ስታሮስቲን <ቢጊኒንግስ ኦፍ ቶፕ ሌቭል ፉትቦል> በሚለው መጽሃፉ ውስጥ እንዳሰፈረው ይህ ውሳኔ ይሁንታ አላተረፈለትም፤ በቡድኑ ውስጥ የመሃል ተከላካይ አማካይ ሆኖ የሚጫወተው አንድሬይ የተባለው ወንድሙም ከፍተኛ ተቃውሞ አነሳበት፡፡ ” ‘በመላው ሶቭየት ህብረት ዝነኛ እንድሆን ትፈልጋለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ቀጠለና ‘ የምተነፍስበት ቦታ እያሳጣኸኝ እንዳለህ እወቅ! በማጥቃቱ ሒደት ማን እገዛ ያደርጋል? ለዘመናት የተጠቀምንበትን የእግርኳስ ታክቲክ እያወደምክ ነው፡፡’ ሲልም አምባረቀብኝ፡፡” ይላል፡፡

በእርግጥ በስፓርታ ሶስተኛ ተከላካይ ተጫዋችን
/Third Backs/ መሞከር አዲስ አልነበረም፡፡ ከሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ ወደ ኖርዌይ የተጓዙ ሰሞን የተጫዋቾች ጉዳት የተለመደውን 2-3-5 ፎርሜሽን እንዳይተገብሩ አስገድዷቸው ታይቷል፡፡ ከ<ስታሮስቲን ወንድማማቾች> መካከል አንዱ የሆነው አሌክሳንደር ስታሮስቲንም ”በወቅቱ ክለባችን ከተለመዱት ሁለት የኋላ ተካላካዮች (Backs) በተጨማሪ ሌላ አንድ የተከላካይ መስመር ተጫዋች (Half-Back) አሰልፎ ጥብቅ የመከላከል ስርዓት የታከለበት የW-M ፎርሜሽንን ለመተግበር ሞከረ፡፡ የግድ ሲሆንም ከመሃል አጥቂው (Center-Forward) ግራና ቀኝ የሚጫወቱት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Insides) ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ይደረግ ነበር፡፡” ሲል የጊዜውን ሁኔታ ያወሳል፡፡ በዚህ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርና የሚና ትግበራ
ተበረታተው ለ1936ቱ የጸደይ ውድድር ዘመን ለመዘጋጀት የሶስተኛው ተከላካይ (Third Back) ሙከራን ገፉበት፡፡ ” ያ ጥገናዊ የለውጥ እርምጃ ድፍረት የተሞላበት ቢሆንም በሃገሪቱ ግን ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም፤ በወዳጅነት ግጥሚያ ዳይናሞ ሞስኮ 5-2 ሲያሸንፈን ደግሞ  የእግርኳሱ አካላት ይህን ስልት ጭራሹኑ አንቅረው ተፉት፡፡ አሁን ደግሞ ይኸው ሁለተኛውን ሙከራ ልናደርግ በዝግጅት ላይ ተገኘን፤ በድጋሚ በወዳጅነት ጨዋታ ቢሆንም ይህኛው ግን እጅግ ወሳኝ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ነው፤ እናም ትልቅ ኃላፊነት ተሸክመን በቀጭኗ ገመድ ላይ ለመራመድ እየጣርን ተገኘን፡፡” ይላል ኒኮላይ ስታሮስቲን፡፡

ስፔንን ከወከሉት ባስኮች ጋር የሚደረገው ጨዋታ ስፖርታዊ ከሆነ ቅኝት ውጪም ትኩረት አገኘ፡፡ የሃገሪቱ ባለ ስልጣናት ለግጥሚያው የገዘፈ አጽንኦት ሰጡ፤ ጨዋታውን በማደራጀት በኩልም የበኩላቸውን መወጣት ጀመሩ፡፡ የሃገሪቱ ስፖርትና ባህል ኮሚቴ ሊቀመንበር ኢቫን ክኻርቼንኮ፣ የኮምሶሞል (የወጣት ኮሚዩኒስቶች ድርጅት) ዋና ሹም አሌክሳንደር ኮሳሬቭ እና ሌሎች በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በስፓርታ የልምምድ ማዕከል ታራሶቭካ ማረፊያቸውን አበጃጁ፡፡ ኒኮላይ ስታሮስቲን <ፉትቦል ስሩ ዘ ይርስ> በሚለው ግለ ታሪክ መጽሃፉ ” ሰዎቹ የመጨረሻ ተስፋቸውን ስፓርታክ ላይ ጣሉ፤ ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን ውጪ ሆኑ፤ የሚያበረታቱን እና መልካም እድሎችን የሚመኙ የማያባሩ የስልክ ጥሪዎች አጨናነቁን፤ በርካታ ደብዳቤዎች ይላኩ ጀመር፤ የቴሌግራም መልዕክቶችም እንደ ጎርፍ ተዥጎደጎዱ፤ ሁሉም ቀናው እንዲገጥመን ተመኘ፡፡ በተለያዩ እርከኖች የሚገኙ የበላይ አካላት የጠሯቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ስብሰባዎች ላይ እንድገኝ ተደረገ፤ ሁሉም አካላት ሃገሪቷ የእኛን ድል በጉጉት እየጠበቀች እንደሆነ ይገልጹ ነበር፡፡” ሲል የወቅቱን ግለት ያስታውሳል፡፡

ይሁን እንጂ ዕለቱ ለሩሲያውያኑ ቀና ሆኖ አልጀመረላቸውም፡፡ በከተማይቱ በተፈጠረ የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ስፓርታክ መንገድ ላይ አሰልቺና አድካሚ ቆይታን እንዲያደርግ ተገደደ፡፡ ጨዋታውም በታቀደለት ሰዓት ሊካሄድ አልቻለም፡፡ ዘግይቶ በጀመረው ግጥሚያ የመጀመሪያ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ካንድም ሁለቴ የመምራት እድል ገጠማቸው፤ ነገር ግን ባስካውያኑ ውጤቱን አቻ ለማድረግ አልቦዘኑም፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ ሃምሳ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን አወዛጋቢ ፍጹም ቅጣት ምት ሺሎቭስኪ ወደ ጎልነት ከቀየራት በኋላ ነገሮች ተቀየሩ፡፡ በሒደት ሶቭየቶቹ ይበልጡን ተጠናከሩ፤ ከዚያም ቭላድሚር ስቴፓኖቭ ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ሩሲያኖቹ 6-2 በሆነ ሰፊ ውጤት ጣፋጭ ድል አስመዘገቡ፡፡ ከጊዜያት በኋላ ኒኮላይ ስታሮስቲን በዕለቱ ያልተለመደ ሚና ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የገባው ወንድሙ በጨዋታው ያሳየው ብቃት እጅግ አስገራሚ እንደነበር ወተወተ፤ ጋዜጦችና የቡድኑ በረኛ አናቶሊ አኪሞቭ ግን ክርክሩ ፍጹም አልተዋጠላቸውም፡፡ የባስኮቹ የመሃል አጥቂ ላንጋራ በአየር ላይ ኳሶች ብልጫ ወስዶበት እንደዋለና ከተቆጠረባቸው ግቦች አንደኛውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ እየጠቀሱ የኒኮላይን ሐሳብ አጣጣሉ፡፡

ያ የባስኮች ሽንፈት በሩሲያውያኑ ዘንድ ነባራዊውን እውነታ የመሳት ስሜት ፈጠረ፡፡ ባስካውያኑ በተከታታይ ዳይናሞ ኪዬቭን፣ ዳይናሞ ቲቢሊሲንና ጆርጂያን የወከለ ቡድን አሸነፉ፡፡ ከዚያም <ፕራቫዳ> የተባለ ጋዜጣ ላይ ቁጣ አዘል ጽሁፍ ለማውጣት ተገደደ፡፡ ተጫዋቾቹ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ በሚማጸነው የጋዜጣው ርዕሰ አንቀጽ ላይ ” የሶቭየት ተጫዋቾች ፍጹም የማይበገሩ መሆን አለባቸው፤ የባስክ ግዛት ቡድን በሶቭየት ህብረት ያሳየው ብቃት የእኛ ምርጥ የሚባሉት ቡድኖች እንኳ በእግርኳስ ከላቀው ደረጃ ወደ ኋላ እጅጉን እንደራቁ አመላክቷል፡፡ ከሌሎች ሃገራት በላቀ በመንግስትና ፓለቲካዊ ፓርቲዎች እንክብካቤ፣ ልዩ ትኩረትና ፍቅር ያደጉ በርካታ ወጣቶች በሃገራችን ከመኖራቸው አኳያ የሶቭየት እግርኳስ ድክመት በቸልታ የሚታለፍ አይደለም፡፡” ሲል ተግሳጻዊ ሃሳቡን አሰፈረ፡፡

በጽሁፉ ከቀረበው ትምክህታዊ አተያይ ጎን ለጎን የሚታይ እውነታም ነበር፡፡ ጽሁፉ ይቀጥላል፥ ” የሶቭየት ቡድኖችን ብቃት ለማሻሻል ከሌሎች ጠንካራ የእግርኳስ ሃገራት ጋር የሚካሄዱ ግጥሚያዎች ላይ መንተራሱ ግልጽ ነው፡፡ ከባስኮች ጋር የተከናወነው ጨዋታም ተጫዋቾቻችንን በብዙ መንገድ (ስኬታማ የረጃጅም ርቀት ቅብብሎች ፣ በመስመሮች የመጫወት ዘዴና ኳስን በግንባር የመግጨት ልምድ እንዲቀስሙ) ጠቅሟቸዋል፡፡” አለ ርዕሰ አንቀጹ በመደምደሚያው፡፡

ከአራት ቀናት በኋላ ባስኮች የፕራቫዳ ጋዜጣን ወሳኝ ነጥቦች ይበልጥ አረጋገጡ፡፡ በሶቭየት ጉብኝት የመጨረሻ በሆነው ጨዋታቸው የሚንስክ ምርጥ አስራ አንድን 6-1 ረመረሙ፡፡ የባስካውያን እግርኳሳዊ ትምህርት ግን የሚዘነጋ አልሆነም፤ W-M ፎርሜሽን በዓለምአቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሃገራት ብሄራዊ ቡድኖች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ ቢወስድበትም በርከት ያሉ ማራኪ የታክቲክ አማራጮች ቀርበውበታል፡፡

ከዚያን ጊዜው የሃገሪቱ (ሶቭየት) እግርኳስ ባለሙያዎች መካከል ታክቲክን በጥልቀት የመረዳት ከፍተኛ ጉጉት ያደረበት ቦሪስ አርካዲዬቭ ነበር፡፡ ቀደም ሲል በጨዋታው ዙሪያ በሚያነሳቸው ሃሳቦቹ እና ለዝርዝር ጉዳዮች ባለው እይታ ከበሬታን ማትረፍ የጀመረው ቦሪስ ቀስበቀስ ራሱን በሶቭየት የመጀመሪያው የእግርኳስ ታክቲክ ኅልዮተኛ (Theorist) ለማድረግ በቃ፡፡ በ1946 ያሳተመው <ታክቲክስ ኦፍ ፉትቦል> የተሰኘው መጽሃፉ በምስራቅ አውሮፓ የሚገኙ አሰልጣኞች ለበርካታ ዓመታት እንደ መመሪያ ድርሳናቸው ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)

error: