ሪፖርት | ስሑል ሽረ በሳሊፍ ፎፋና ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፈ

የ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ጅማሮን ሲያደርግ ስሑል ሽረ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በመርታት ላለመውረድ በሚያደርገው ትንቅንቅ ቀጥሏል፡፡

በመቐለ ባሳለፍነው ሳምንት ሽንፈት የገጠመው ስሑል ሽረ በአምስት ተጫዋቾች ላይ ቅያሪን አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ሰንደይ ሮቲሚ፣ አሳሪ አልመሐዲ፣ ዲሚጥሮስ ወልደሥላሴ፣ ክብሮም የማነ እና ሐብታሙ ሸዋለምን በማሳረፍ ዳዊት አሰፋ፣ ዮናስ ግርማይ፣ ብሩክ ተሾመ፣ ደሳለኝ ደበሽ እና ሙሉዓለም ረጋሳ ተተክተዋል። በሸገር ደርቢ ያለ ግብ አጠናቆ በመጣሁ ኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ በወንድወሰን አሸናፊ እና አማኑኤል ዮሐንስ ምትክ ኢስማኤል ዋቴንጋ እና ሳምሶን ጥላሁንን ወደ ሜዳ አስገብተዋል፡፡

ስሑል ሽረዎች ብልጫን በወሰዱበት ጨዋታ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉበት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዝግ የመከላከል አደረጃጀትን በመጠቀም በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩበት ነበር፡፡ 2ኛው ደቂቃ ላይ ሳሊፍ ፎፋና በረጅሙ ከሙሉዓለም የተላከለትን በቀጥታ መትቶ ኢላማዋን ሳጠብቅ ስትወጣ ቢስማርክ  አፒያ 10ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ኢላማውን ያልጠበቀ የግብ ሙከራን አድርጓል። 

ቀስ በቀስ የሽረን አጨዋወት የተረዱት ቡናማዎች በመልሶ ማጥቃት ተስቦ በመጫወት የጨዋታውን የመጀመሪያ ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ አድርገዋል፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ ከግብ ጠባቂው ዋቴንጋ በረጅሙ የተለጋን ኳስ ወደ መሬት በማውረድ አክርሮ ቀጥታ ወደ ግብ ቢመታም ለጥቂት በአግዳሚው ተጨርፎ ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ከዚህች ሙከራቸውም በኃላ መልሶ ማጥቃት አዋጪ የሆነላቸው ቡናማዎች ይበልጥ ተጭነው በመጫወት የስሑል ሽረ ተከላካዮች ማስጨነቅ ችለዋል፡፡ 28ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደምሱ የሰጠውን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም የስሑል ሽረ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት መዘናጋታቸውን ተከትሎ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር  ያገኘውን ግልፅ የግብ አጋጣሚ ዳዊት አሰፋ በግሩም ሁኔታ አስጥሎታል። ኃይል ላይ ባመዘነው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሽረዎች በቢስማርክ አፒያ መልካም አጋጣሚን ቢያገኙም ዋቴንጋ አውጥቶበታል።

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ መልኩ ቀዝቀዝ ብሎ በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት እና ንትርክ ሲቀጥል ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ያላቸውን ኃይል በጨዋታው ሲጠቀሙ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ስሑል ሽረዎች ጎል ማስቆጠር ችለዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ዩጋንዳዊው አማካይ ያስር ሙገርዋ በድንቅ ሁኔታ ተጫዋቾችን በማለፍ የሰጠውን ለስሑል ሽረ ማንሰራራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ሳሊፉ ፎፎና ወደ ግብ በመምታት አስቆጥሮ ሽረን መሪ ማድረግ ችሏል። ፎፋና ቡድኑን በግማሽ ዓመት ከተቀላቀለ ወዲህ 6 ጎሎችን በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ ሽረዎች ተጨማሪ ለማከል ሙከራ ሰለያደርጉ ኃይሌ ገብረትንሳኤን አስወጥተው የኃላሸትን ያስገቡት ቡናማዎችም አቻ ለመሆን ጥረትን አድርገዋል፡፡ በተለይ ተቀይሮ እንደገባ የኋላሸት በቀጥታ መትቶ ለጥቂት አምልጣዋለች። ጨዋታው በስሑል ሽረ 1-0 መጠናቀቁን ተከትሎ ሽረዎች ነጥባቸውን 22 ቢያደርሱም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አሁንም የሌሎች ውጤትን በቀጣይ ሳምንታት ለመጠበቅ ይገደዳሉ። ቡናዎች በአንፃሩ በ33 ነጥብ በነበሩበት 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡