የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ለ ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ሲደረጉ አዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ዕሁድ ረፋድ በአበበ ቢቂላ ስታድየም አዳማ እና አፍሮ ፂዮን በተገናኙበት ጨዋታ መጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ ቢችሉም ጥረታቸው በአፍሮ ፂዮን ተከላካዮች ሲጨናገፍባቻው ነበር። አዳማዎች ከመስመር በመነሳት ወደ መሀል እየገቡ በማጥቃት ጫና የፈጠሩ ሲሆን 10ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ ሳጥን ጠርዝ የተሻገረለትን ኳስ ቢኒያም አይተን ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት የቡድኑ ቀዳሚ ሙከራ ነበር። በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ሚና የነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ በግራ መስመር ሰጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ ከግብ ጠበቂ ጋር ተገናኝቶ ለቡድን አጋሩ አሻግራለሁ ሲል በተከላካዮች የተመለሰበትም ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ሲሆን የአብስራ አክሊሉ ወደ ግብ የመታቸው ሁለት ኳሶችም ጥሩ የሚባሉ የቡድኑ ጥረቶች ነበሩ።

ከመሐል ወደ ሳጥን  ጠርዝ በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶችን በመቆጣጠር የተሻለ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ ከመሀል የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ድንቅ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ዱሬሳ የግል ተሰጥኦውን በሚያሳይ መልኩ ከሳጥን ውጪ ያገኝውን ኳስ ሦስት ተከላካዮችን አልፎ ሳጥን ውስጥ በመግባት ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያው አጋማሽ የመሀል እና የአጥቂ ክፍላቸው ላይ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት አፍሮ ፂዮኖች የተሻለ ተጭነው በመጫወት ረጃጅም ኳሶችን በመጣል የአዳም ከተማን ተከላካዮች ሰብርው ለመግባት ጥረት ቢያደረጉም እምብዛም አልተሳካላቸውም። ጭማሪ ደቂቃ ላይ ግን እንድሪያስ ለገሰ ሰጥን ውስጥ  የተገኝውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 2 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ ጨዋታዎች አዲስ አበባ ከተማ አሰላ ኅብረትን 4-0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ መድን 3-3 ፤ ሀላባ ከተማ ከፋሲል ከተማ 0-0 ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡