ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ በጅማ በሁለት ግብ ከመመራት ተነስቶ ወሳኝ አንድ ነጥብ አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ተጠባቂ ከነበሩት ጨዋታዎች አንዱ የነበረው የጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ጅማዎች በ25ኛው ሳምንት በፋሲል ከተማ ከባድ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ውስጥ ለዛሬው ጨዋታ ዘሪሁን ታደለን በዳንኤል አጄ፣ መላኩ ወልዴን በከድር ኸይረዲን፣ ብሩክ ገብረአብን በኦኪኪ አፎላቢ በመተካት ቀርበዋል፡፡

መቐለ 70 እንደርታ በተመሳሳይ በ25ኛው ሳምንት በሜዳው በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ ውስጥ አራት ለውጦችን አድርጓል። በዚህም መሰረት ሶፎንያስ ሰይፉን በፊሊፕ ኦቮኖ፣ አንተነህ ገ/ክርስቶስን በአንዶህ ክዌኩ፣ ያሬድ ከበደን በሐይደር ሸረፍ፣ ያሬድ ብርሃኑን በኦሌይ ማዊሊ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በዋና ዳኛ ብርሃኑ መኩርያ ዳኝነት የተመራው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ቀዝቃዛና እምብዛም ፉክክር ያልነበረበት ነበር ባለመዳዎቹ በግራና በቀኝ መስመሮች ከሚነሱ ኳሶች የመጥቃት ምርጫቸውን ሲያደርጉ በአብዛኛዎቹ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሞኣም አናብስቶቹ ከሐይደር ሸረፋ በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ኳሶች ወደ ጅማ የግብ ክልል ለመድረስ ሞክረዋል።

የግብ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ጅማዎች ሲሆኑ በ5ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። በመቐለ በኩል በ10ኛው ደቂቃ ኦሴይ ማዊሊ ከቀኝ መስመር አክርሮ ወደ ግብ የመታው ተከላካዮችን ጨርፋ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለቆመው ዩናስ ገረመው ብትደርስም ዮናስ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በ31ኛው ደቂቃ የመቐለ 70 እንደርታው ሐይደር ሸረፋ በጎድን አጥንቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ሄኖክ ኢሳይያስ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡

ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ከሳጥን ውጭ በኦኪኪና በማማዱ ሲዲቤ አማካኝነት ከርቀት ሙከራዎችን ቢያደርጉም በጨዋታው የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በመቐለው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ33ኛው ደቂቃ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ወደ መሐል እያሰፍ ሄዶ ከሳጥን ውጭ የሞከረው ሙከራ በዳንኤል አጄ ተይዞበታል፡፡ ከሐይደር በጉዳት ከወጣ በኃላ መቐለዎች የማጥቃት አማራጫቸውን ወደ ቀኝ መስመር በማዘንበል ከመስመር በሚሻገሩ ተሻጋሪ ኳሶች በመጠቀም ቢጫወቱም ስኬታማ አልነበሩም። በ42ኛው ደቂቃ ዮናስ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ማዊሊ መሬቱ አዳልጦት ያልተጠቀመው አጋጣሚ የሚያሰቆጭ ነበር። ጅማዎች በመጀመርው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በማማዱ ሲዲቤ የሞከሯቸው አደገኛ ሙከራውች ፊሊፕ ኦቮኖ ያዳነበት እና በግቡ አናት ላይ የሰደደው አጋጣሚ ባለሜዳዎቹን መሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የተለየና ቶሎ ቶሎ የግብ ሙከራዎች የተደሰጉበት፤ ለመሸናነፍ የተደረገ ፉክክርም የተስተዋለበት ነበር። በዕለቱ የተቆጠሩት አራት ግቦችም ከእረፍት መልስ የተቆጠሩ ነበሩ። መቐለዎች በተሻጋሪ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ጅማ ግብ ክልል መድረስ ሲችሉ ጅማዎች በመልሶ ማጥቃት እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በ50ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ኦኪኪ ላይ የተሰራውን ጥፋት ማማዱ ሲዲቤ ወደ ግብ ሲሞክረው ኳሷ የመቐለን ተከላካዮች ጨርፋ የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ዲዲየ ለብሪ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ፡፡

መቐለ 70 እደርታዎች የሚጠቀሟቸው ተሻጋሪ ኳሶች እብዛም ውጤታማ አልነበሩም በ65ኛው ደቂቃ አማኑኤል የጅማን ተከላካዮች አምልጦ ገብቶ ዳንኤል ያዳነበት ሙከራ ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን በተቃራኒው ኳሶቹ ተመልሰው በመልሶ ማጥቃት ጫና ሲፈጥሩባቸው ነበር። በ68ኛው ደቂቃ ከመሐል ኦኪኪ ለማማዱ ሲዲቤ የሰጠውን ኳስ ማሊያዊው አጥቂ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ወደ መሐል አስፍቶ ገብቶ ያስቆጠራት ግብ ባለሜዳዎቹን በሁለት ግል ልዩነት እንዲመሩ አስችላለች። ከግቦቹ መቆጠር በኃላ በይበልጥ የተነቃቁት ጅማዎች የጎል ልዩነቱ ሊያሰፉባቸው የሚችሏቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም። ሲዲቤ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበትም የሚጠቀስ ነበር፡፡

በ77ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ያሬድ ተጫዋቾችን አታሎ ወደ መሀል ያሻገረውን ኳስ ተከላካዮች ተመልሳ ከግቡ ፊት ለፊት የሳጥኑ ውጭ የቆመው ጋብርኤል አህመድ አስቆጥሮ የምአም አናብስትን ተስፋ ያለመለመች ግብ ግብ አስቆጠረ። ተጨማሪ ግብ ለማስቆ ሁለቱም ቡድኖች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ መቐለዎች ጋብርኤል ከርቀት የሚሞክራቸው፤ በጅማዎች በኩል ማማዱ ከፊሊፕ ኦቮኖ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመከነው ጨዋታውን ገድለው ሊወጡ የሚችሉበት አጋጣሚዎች ነበሩ።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መገባደጃ ላይ ጋብርኤል ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ተከላካዮችን ጨርፋ መቐለዎችን ከመሸነፍ ያዳነች ግብ አስቆጠሯል። መቐለዎች ከግቡ መቆጠር በኋላም በፈጠሩት ጫና ውጤቱን ሊቀለብሱ የሚችሉበት አጋጣሚዎች ቢያገኙም በግቡ አግዳሚ እና በዳንኤል አጄ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመቐለ 70 እንደርታ የቡድን መሪና የአሰልጣኞች ስታፍ ከእለቱን ዳኞች ጋር ግብግብ ገጥመው የነበረ ሲሆን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ኮሚሽነሩ ገላጋይነት ግብግቡን አስቁመውታል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ መቐለ 49 አድርሶ ነጥቡን ከፋሲል እና ሲዳማ ጋር ነጥቡን አስተካከሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡