ሪፖርት | ወላይታ ድቻ የሊጉ መሪ ፋሲልን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን ርቀት አስፍቷል

ወደ ወራጅ ቀጠናው ላለመግባት ትንቅንቅ ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የሊጉ አናት ላይ የሚገኘው ፋሲል ከተማን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል 25ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አቻ በተለያየበት እና ፋሲል ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ከረታበት ጨዋታ የተጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሶስት የአንድ ቤተስብ ተጫዋቾች በተቃራኒ ክለብ መጨዋታቸው ቀልብ ሳቢ ያደረገው እና ፋሲል በመሪነቱን ለመቀጠል እንዲሁም ድቻ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ተጠባቂ ያደረገው ይህ ጨዋታ ከተጠበቀው አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴን መመልከት ባንችልም ግብ ለማስተናገድ ግን ደቂቃ አልፈጀም። ኳሱ ተጀምሮ በፍጥነት ወደ ወላይታ ድቻ ግብ የደረሰውን ኳስ ታሪክ ጌትነት ተቆጣጥሮ በረጅሙ ሲለጋ ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ እና ከድር ኩሊባሊ በፈጠሩት አለመናበብ አጠገባቸው የነበረው ባዬ ገዛኸኝ በጭንቅላቱ ገጭቶ ግብ በማድረግ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም የሜዳ እንቅስቃሴ ያላየንበት ይህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ከየትኛውም አቅጣጫ የሚገኟቸውን ኳሶች በረጃጅሙ እያሻገሩ የፊት አጥቂያቸው ባዬ ገዛኻኝ አነጣጥረው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃሩ ዐፄዎቹ ኳስ ለመቆጣጠር አስበው በተለይም ደግሞ ከሱራፌል ዳኛቸው በሚነሱ ኳሶች ሦስቱንም አጥቂዎች ኢዙ አዙካ፣ መጂብ ቃሲም እና ሽመክት ጉሳን በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ቢደርጉም ሜዳው ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት አመቺ ስላልነበር ውጤታማ አልነበረም።

በዚህ ጨዋታ የሁለቱም ቡድን የተከላካይ መስመር ጉልህ የሚባሉ ስህተቶችን ሲሰሩም የተስተዋለ ሲሆን የፋሲል የአቻነት ጎል መነሻም ተክሉ ታፈሰ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለታሪክ ጌትነት ሲያቀብል ኳሷ የማጠሯ ምክንያት የተገኘ ነበር። አጋጣሚውንም በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ኢዙ አዙካ ታሪክ ጌትነት ከመድረሱ በፊት በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።

ቅብብሎቻቸው ስኬታማ ያልነበረው የጦና ንቦች አልፎ አልፎ ወደ ጎል ለመድረስ ግን አልተቸገሩም። 28ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰመድ ዓሊ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ቸርነት ጉግሳ በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ የግሉን ብቃት ተጠቅሞ ሰብሮ በመግባት ሲሞክር ሚካኤል ሳማኪ ተወርውሮ ለጥቂት ያወጣትም ለግብ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ኢዙ አዙካ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኤፍሬም ዓለሙ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በጣቶቹ ለጥቂት ነክቶ በአግዳሚው ያወጣትም የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ በአቻ ውጤት ለእረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጦና ንቦች በረጃጅም ኳሶች አጨዋወታቸው ሲቀጥሉ ፋሲሎች ከመጀመርያ ግማሽ አጨዋወታቸው በተለየ መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው የፊት አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲምን ወደ መሀል ተከላካይነት በመመለስ በረጃጅም ኳሶች ለመጫወት አልመው ገብተዋል። ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ መስመር የላከለትን ኳስ በረከት ወልዴ ሁለት ተጫዋቾች አታሎ ሞክሮ በአግዳሚው ለጥቂት የወጣችው ኳስ የምትጠቀስ ጥሩ ሙከራ ነበረች። ወላይታ ድቻዎች ቸርነት ጉግሳን አስወጥተው ኃይሌ እሸቱን ካስገቡ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል በመድረስ ተከላካዮችን ሲያስጨንቁ ተስተውሏል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ከ30 ሜትር ርቀት የተገኘችውን የቅጣት ምት ሄኖክ አርፊጮ ሲያሻማ አብዱልሰመድ ዓሊ በጭንቅላቱ ገጭቶ ከድር ኩሊባሊ እንደምንም ተንሸራቶ አውጥቶበታል።

በመጀመሪያው ግማሽ በተለይ በአብዱልሰመድ ዓሊ ሲሰሩ የነበሩትን የቅብብል ስህተትች የቀረፉት ዲቻዎች የመሀል ክፍላቸው ጥሩ እንዲሆንላቸው አድርጓል። 67ኛው ደቂቃ አብዱልሰመድ አሊ በረጅሙ የላካትን ኳስ ኃይሌ እሸቱ በጭንቅላቱ ገጭቶ በአግዳሚው ስትወጣ ከዝች ሙከራ በኋላ ባዬ ገዛኻኝ ከሳጥን ውጭ ያገኘውን ነፃ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ በሳማኪ ጥረት ስትመለስ ያገኛትን ኳስ ኃይሌ እሸቱ ለጥቂት በአግዳሚው ወጥታበታለች። በሁለኛው አጋማሽ የሚጠበቀውን ያህል አስፈሪ ያልነበሩት ዐፄዎቹ የተቃራኒ ግብ ከመፈተሽ ግን አልቦዘኑም።

ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ያወጣበት ለግብነት የተቃረበች ሙከራ ነበረች። በአብዛኛው ከግራ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አርፊጮ ሲሻገሩ የነበሩት ኳሶች ዲቻዎች ጫና እንዲፈጥሩም አግዟል። 75ኛው ደቂቃ ሄኖክ አርፊጮ በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ ኃይሌ እሸቱ በጭንቅላቱ ገጭቶ ማራኪ ግብ በማግባት ቡድኑን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ድቻዎች ውጤታቸውን ለማስጠበቅ አፈግፍገው ሲጫወቱ በአንፃሩ ፋሲሎች ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል። ተቀይሮ የገባው አብዱራሕማን ሙባረክ እና ተክሉ ታፈሰ 87ኛው ደቂቃ ተጋጭተው ጉዳት በማስተናገዳቸው ጨዋታውን መቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ፋሲል ከተማዎች ቅያሪ ጨርሰው ስለነበር በጎደሎ ለመጫወት ሲገደዱ ድቻዎች ግን አንቸነህ ጉግሳን አስገብተዋል። በዚህ መሰረት ጨዋታው ወላይታ ድቻ 2-1 በሆነ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ድቻ በድሉ ነጥቡን 31 አድርሶ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን ርቀት አስፍቷል። ፋሲል በአንፃሩ መቐለ አቻ በመውጣቱ፣ ሲዳማ ደግሞ በማሸነፉ በእኩል 49 ነጥቦች የሊጉን መሪነት በጎል ልዩነት በልጦ መምራቱን ቀጥሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡