አአ U-17 | መድን በአዳማ ሲሸነፍ ኤሌክትሪክ ከመሪው ያለውን ልዩነት አጥብቧል

የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር የ15ኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ሀሌታ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቷቸዋል።

03:00 በአካዳሚ ሜዳ ኢ/ወ/ስ/አካዳሚ ከ መከላከያ ያገናኘው ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክቶን ያለ ጎል 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው የመጀመርያ 15 ደቂቃዎች መከላከያዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም በጎሎች ያልታጀበ በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው በዚሁ መቀጠል አልቻለም። በአንፃሩ አካዳሚዎች የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ በመግባት በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የጎል ዕድል ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላካያዎች በኩል በአንድ አጋጣሚ አጥቂያቸው ምስጋናው መላኩ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ከቀረው ካልሆነው በቀር በአካዳሚ ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር። በተለይ በአካዳሚ በኩል ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል ከድር ዓሊ ሳይጠቀምባቸው የቀሩት ኳሶች የሚያስቆጩ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ቢሆንም ጎል ሳይቆጠርበት ያለ ጎል 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዚሁ በአካዳሚ ሜዳ 05:00 በቀጠለው ተጠባቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በየትኛውም የዕድሜ እርከን ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ የሚኖረውን ጠንካራ ፉክክር በዛሬም ጨዋታ አስመልክቶናል። ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል ብንመለከተም በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ፈረሰኞቹ የተሻሉ ነበሩ። ፈረሰኞቹ ጎል የማግባት ጥረታቸው ተሳክቶ ልማደኛው አጥቂያቸው ፀጋዬ መላኩ በድንቅ አጨራረስ ጎል አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የመሐል ሜዳ ስፍራ ተጫዋቾቻቸው ከሚያደርጉት መልካም እንቅስቃሴ በቀር በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወደ ጎል ለመድረስ ተቸግረው የነበረ ቢሆንም የመሐል ሜዳ ተጫዋቹ ቢንያም አጠንክሮ ከርቀት የመታውን ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብጠባቂ የኔነህ ታምራት ሲተፋው ሚኪያስ ቡልቡላ በፍጥነት በመድረስ ባስቆጠረት ጎል ኢትዮጵያ ቡናዎች አቻ መሆን ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ ፈረሰኞቹ የማሸነፊያውን ጎል እስካስቆጠሩበት ጊዜ ድረስ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ቢያስመለክቱንም ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ጎል ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው እዮብ መርሻ ከርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎልነት በመቀየር ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊ የሆነበትን ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

09:00 ጃንሜዳ በተካሄደው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ተገናኝተው በአዳማ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በርከት ያለ የስፖርት ቤተሰብ የተመለከተውና ብርዳማ አየር ጨዋታው ቢካሄድም የኳሱ ፍሰት እና ጥሩ እንቅስቃሴ ተመልካቹን ቁጭ ብድግ በማድረግ ተጠናቋል። የፊት መስመር አጥቂዎቻቸው እግራቸው ኳስ ሲገባ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት በመሄድ ጫና በመፍጠር የሚታወቁት አዳማዎች ዛሬም እንደተለመደው የኢትዮጵያ መድንን ተከላካዮችን ሲፈትኑ ውለዋል። ይህም ጥረታቸው ተሳክቶ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት የገቡት አዳማዎች ነቢል ኑሪ ባስቆጠረው ጎል አዳማዎች ቀዳሚ መሆን ቻሉ። ብዙም ሳይቆይ የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥት ያደረጉት መድኖች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ጌታሁን ካሳይ ወደ ጎልነት በመቀየር አቻ አድርጓቸዋል። ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታ በስፍራው የነበረን ተመልካች ያስደሰተ ሆኖ ሲያልፍ ከመስመር በሚነሱ ኳሶቻቸው አደጋ ይፈጥሩ የነበሩት አዳማዎች ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ልማደኛው አጥቂ ፍራኦል ጫላ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ ጉሽሚያ እና ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት የቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች የአቻነት ጎል አልያም ለማሸነፍ ጎል ፍለጋ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበት በአንፃሩ አዳማዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ጎል በማስቆጠር ጨዋታውን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ጥረቶች ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ አስመልክቶን በሁለቱም በኩል ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት ጨዋታ በአዳማ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጎፋ ሜዳ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ አፍሮ ፅዮንን 1-0 በማሸነፍ ከመሪው ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን ነጥብ የሚያጠብበትን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቶ ወጥቷል። በሌላ ጨዋታ ሀሌታ ሠላምን 3-2 አሸንፏል።

16ኛ ሳምንት

ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2011

አካዳሚ ሜዳ
03:00 ኢትዮጵያ መድን ከ ኢ·ወ·ስ·አካዳሚ
05:00 አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤክትሪክ

ጎፋ ሜዳ
03:00 መከላከያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
05:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀሌታ

ጃልሜዳ
09:00 አፍሮ ፅዮን ከ ሠላም


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡