የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 2-1 ፋሲል ከተማ

ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ የሊጉ መሪ ፋሲል ከተማን አስተናግዶ በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተየያተቸውን ሰጥተውናል።

“ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾች ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ቀይረውልኛል” አሸናፊ በቀለ (ወላይታ ድቻ)

ስለጨዋታው

አጀማመራችን በጣም ጥሩ ነበር። ያሰብነው በመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃ ግብ ማግባት ነበር አግብተናል። ፋሲል በዚህ ዓመት ጥሩ ከሚባሉት ቡድኖች መካከል አንዱ ነው። እኛ ላይ ያገቡብን ግብ የተጫዋቾቼን በራስ መተማመን አበላሽቶብኛል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሰላሳ ደቂቃዎች ጥሩ አልነበርንም። ያንን ስህተት በሁለተኛው ግማሽ አርመን ተቀይረው የገቡት ልጆች ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ቀይረውልኛል።

የተከላካዮች ጉልህ ስህተት

የሚስተካከሉ ነገሮች አሉ። የኛ ቡድን መጀመሪያም ብዙ ነጥብ የጣለው ከተከላካይ ስህተት የተነሳ ነው። ከደጉ ደበበ ጋር ለማጣመር ሁለት ሶስት ተጫዋቾችን ነው እያቀያየርኩ እየተጠቀምኩ ያለውት። ይህ ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው። አሁን በዘዴ ያሉትን ጠጋግነህ መጫወት ነው። ለዛም ነው በአምስት ተከላካዮች ስጫወት የነበረው።

ረጃጅም ኳሶችን ስለመምረጣቸው

የፋሲል አጨዋወት በኳስ ንክኪ የተመሰረተ ነው። ረጃጅም ኳሶችን ለመጫወት ያሰብነውም የአማካይ ክፍላቸውን ለመቁረጥ ነው።

“ውጤቱ ላይ ነው እንጂ ያተኮርነው ለተመልካች ጥሩ እግር ኳስ አላሳየንም” ውበቱ አባተ (ፋሲል ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው ለተመልካች ብዙም ያስደሰተ አልመሰለኝም። እነሱ ካሉበት ቦታ አንፃር እና እኛም መሪነታችን ለማስቀጠል በሁለታችንም በኩል ውጥረት ነበር። ውጤቱ ላይ ነው እንጂ ያተኮርነው ለተመልካች ጥሩ እግር ኳስ አላሳየንም። ጎሎቹ የገቡበት መንገድ ለኛ ብዙም ደሰ የሚል አይደለም። ዞሮ ዞሮ በሜዳቸው እንደመጫወታቸው ጥሩ ነበሩ አሸንፈዋል።

የተከላካዮች ስህተት

በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ የኛ ቡድን አለ። እዚህ ሜዳ ላይ ስህተት ባይሰሩ ይገርመኝ ነበር። ምክንያቱም ሜዳው አመቺ አይደለም። ጥሩ ነገሩ ሁል ግዜ እዚህ ሜዳ አይደለም የምንጫወተው። ስለዚህ ለወደፊቱ እንደዚህ አይነት ስህተቶች ይኖራሉ ብዬ አላስብም። አንድ ከሜዳ ጋር የማይያያዝ አለመናበብ ችግር ነበር። እሱም ያጋጥማል። ጠንካራ የመከላከል መስመር ስላለን አንሰጋም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡