የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በድራማዊ መልኩ ሲጠናቀቅ ኤስፔራንስ ቻምፒዮን ሆኗል

በአወዛጋቢ ሁኔታ ባልተጠናቀቀ ጨዋታ ፍፃሜውን ባገኘው የ2018/19 ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ኤስፔራንስ ደ ቱኒስ በድምር ውጤት ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብን 2-1 አሸንፎ ለተከታታይ ዓመት ቻምፒዮን ሆኗል።

በመጀመርያው ጨዋታ 1-1 የተጠናቀቀው ይህ ፍልሚያ የመልስ ጨዋታ በኤስፔራንስ ሜዳ አርብ ምሽት ሲካሄድ ባለሜዳው ቡድን የሱፍ ቤላይሊ በ41ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል 1-0 እየመራ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሆኖም ጨዋታው ከእረፍት መልስ የቀጠለው ለ15 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ59ኛው ደቂቃ ዋሊድ ኤል ካርቲ ዋይዳድን አቻ የምታደርግ ጎል ቢያስቆጥርም (ጎሉ በቴሌቪዥን ምልሰት ሲታይ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋግጧል) ከጨዋታ ውጪ ተብላ የተሻረች ሲሆን የዋይዳድ ተጫዋቾች የውሳኔው ትክክለኝነትን VAR እንዲረጋገጥ ቢጠይቁም ጨዋታውን የመሩት ፓፓ ባካሪ ጋሳማ ፈቃደኛ ባለመሆን ጎሉ ተሽሮ ጨዋታው እንዲቀጥል ወስነዋል። ይህን ተከትሎም ጨዋታው በውዝግብ እና ምልልሶች ከ1 ሰዓት በላይ ሲቋረጥ ዋይዳዶች ግጥሚያውን ከቆመበት ለመቀጠል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ጋምቢያዊው ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስር ፊሽካ አሰምተዋል። ኤስፔራንስ ደ ቱኒስም በድምር ውጤት 2-1 አሸንፎ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግን ለሁለተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ማሸነፉን አረጋግጧል።

በድራማዊ መልኩ ፍፃሜውን ያገኘው ይህ ጨዋታ በVAR እንደሚታገዝ አስቀድሞ የተገለፀ ቢሆንም በጨዋታው ወቅት ቴክኖሎጂው እክል አጋጥሞት መስራት እንዳልቻለ እና አርቢትሩ የውሳኔውን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ያልቻሉትም ከዚህ መነሻ እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል። የኤስፔራንሱ አምበል ካሊል ኤል ሻማም ከጨዋታው በኋላ ለቤን ስፖርት በሰጠው አስተያየት ደግሞ አርቢቴሩ ቫር ችግር እንዳጋጠመው አስቀድመው መናገራቸውን ገልጿል። ” ዳኛው ለሁለታችንም (ለአምበሎች) ከጨዋታው መጀመር በፊት የቫር ቴክኖሎጂው ችግር እንዳጋጠመውና እንደማይኖር ተናግሯል። ነገር ግን የዋይዳዱ አምበል የዳኛውን ፈረንሳይኛ ንግግር የተረዳ አይመስለኝም።” ” ብሏል።

ይህ የፍፃሜ ጨዋታ የመጀመርያ ጨዋታም በውዝግብ የታጀበ እንደነበር የሚታወስ ነው። ኤስፔራንሶች ያስቆጠሩት የመጀመርያ ጎል ከመቆጠሩ በፊት በነበረ ሒደት ኳሱ በእጅ ተነክቶ ነበር በሚልም ካፍ ግብፃዊው ዳኛ ጋኸድ ግሬሻን ለ6 ወራት አግዷል።

ለአጠቃላይ አራተኛ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ባለ ድል የሆነው ኤስፔራንስ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በመጪው ዓመት ህዳር ለሚደረገው የዓለም ክለቦች ዋንጫ የሚቀርብ ሲሆን በነሀሴ ወር ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊው ዛማሌክ ጋር ለካፍ ሱፐርካፕ ድል የሚፋለም ይሆናል።

error: