ወልዋሎ በርካታ ስራዎች ለመከወን የሚያስችል ድረ ገፅ በመጪው እሁድ ያስመርቃል


ክለቡን የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎች ጨምሮ የደጋፊዎች ወርሃዊ ክፍያ እና ቁሳቁስ በቀላሉ ለመገበያየት እንዲያስቻል ተደርጎ የተሰራ ድረ ገፅ በመጪው እሁድ በፕላኔት ሆቴል በሚደረግ ሥነ-ስርዓት በይፋ ሥራ የሚጀምር ይሆናል።

በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ የኦንላይን ግብይት ያጠቃለለው የመጀመሪያው ይሆናል የተባለው ይህ ድረ-ገፅ በአንበሳ ባንክ በሄሎ ካሽ አማካኝነት በቀላሉ የሚከናወን ሲሆን ለክለቡ ደጋፊ ማኅበር አባላት በርካታ አማራጮች ይዞ የቀረበ መሆኑ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ስለ ቴክኖሎጂው እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኤዲዮ ማኔጅመንት ዋና ዳይሬክተር አቶ አንገሶም ተኽላይ ድረ ገፁ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል። ” በመጀመሪያ ደረጃ ከወልዋሎ ጋር ይሄን ውል ፈፅመን ስራ እንድንሰራ ስለተደረገልን ትብብር እና መልካም ፍቃድ ያለንን አድንቆት መግለፅ እፈልጋለሁ። ይህን የዲጂታል ስፖርት ፕላት-ፎርም ድርጅታችን ሰርቶ ሲያቀርብ ያለምንም ክፍያ መሆኑ ድርጅታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማዋል።” ያሉት አቶ አንገሶም በፕላት ፎርሙ ዙርያ የሚተሉት አምስት ነጥቦች አንስተዋል።

1) አሁን ያለዉ የአባላት ምዝገባ በፅህፈት ቤት እየመጡ የሚደረግ ነው። አዲሱ አሰራር ግን በሞባይል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በያሉበት የግድ ፅህፈት ቤት በአካል ሳይመጡ ዲጅታል የአባልነት ምዝገባ ራሳቸውን መመዝገብ እንዲሁም ደግሞ በሄሎ ካሽ በቀጥታ የአባላት ዲጅታል ምዝገባ ማድረግ የሚችሉበት ነው።

2) የወርሃዊ መዋጮ ከየትኛውም አካባቢ በቀጥታ በሄሎ ካሽ መክፈል የሚችሉበት ስርዓት ነው።

3) ክለቡ ለገቢ ማስገኛ ብሎ የሚሸጣቸውን ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በኦንላይን መሸጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

4) በክለቡ ውስጥ ያሉ ታሪካዊ የፎቶ ክምችትም በዚህኛው ድረገፅ ያገኛሉ።

5) የክለቡ መልዕክቶችም ሆነ ዋና ዋና ዜና በቀላሉ የሚካት ይሆናል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ደጋፊዎችን መመዝገብ እና መዋጮ ለመሰብሰብ የሚስችል ከመሆኑ ባሻገር ደጋፊዎች በሄሎ ካሽ በመጠቀም በቀላሉ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ መፈፀም ይችላሉ። አንበሳ ባንክም ለክለቡ የተመዘገቡ ደጋፊዎች በሄሎ ካሽ አማካኝነት የክለቡ ማልያ ለገዙ የመጀመርያ 500 ደጋፊዎች የ 40% ቅናሽ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል።

በኤዲዮ ቴክኖሎጂ የቀረበው ይህ ዘመናዊና የኦንላይን ግብይት ያጠቃለለው ይህ ድረ ገፅ ከደጋፊነት አባል ከማብዛት ባሻገር ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡