ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ በጋራ ራሳቸውን በገቢ ለማጠናከር ተስማሙ

ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ራሳቸውን በፋይናንስ ለማጠናከር እና በዘለቄታዊነት የገንዘብ እጥረታቸውን ለመቅረፍ የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ።

ይጀመራል ተብሎ ከታሰበበት ሰዓት አንድ ሰዓት ዘግይቶ የተጀመረው ዝግጅት በርካታ ሃሳቦች የተነሱበት ሲሆን ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳይ ተብራርቶበታል። በባህር ዳር ናኪ ሆቴል በተደረገው ዝግጅት የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን ዓየሁ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አዳነ (ዶ/ር)፣ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በፕሮግራሙ ሁለቱን የክልሉ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦችን ፋይናንስ በዘለቄታዊነት ለማጠናከር የታሰበን ፕሮጀክት አስመልክቶ ገለፃ እና ማብራሪያ የተደረገ ሲሆን በዋናነት ክለቦቹ ከመንግስት በየዓመቱ ከሚበጀትላቸው በጀት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ተነግሯል። ምንም እንኳን የስምምነቱ ዋና ዓላማ ክለቦቹን ከመንግስት ጥገኝነት ለማላቀቅ ቢሆንም በአጭር ጊዜ እቅድ ክለቦቹን ህዝባዊ ማድረግ፣ ደጋፊዎችን ያማከለ ስራ መስራት፣ የታዳጊ ማሰልጠኛ ማዕከላትን መገንባት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ያለመ መሆኑ ተነግሯል።


ገንዘቡን የመሰብሰብ ሃላፊነት የየክለቦቹ ደጋፊ ማኅበራት የሚያከናውኑት መሆኑ የተነገረለት ይህ ፕሮጀክት ፋይናንሱን የተመለከተ የወጪ ጉዳዮች ክለቦቹ በሚያዋቅሯቸው ኮሚቴዎች እንደሚሰራ ተብራርቷል። በተለያዩ ፕሮግራሞች የሚሰበሰበውን ገንዘብ እኩል ለመካፈል የተስማሙት ሁለቱ ክለቦች በጋራ ደጋፊዎቻቸውን በማሰልጠን ገቢዎች ከየአቅጣጫው እንዲሰበሰቡ እንደሚያደርጉ ተገልፃል። ከስድስት ወር በላይ እንደፈጀበት የተገለፀው ፕሮጀክቱ የተለያዩ ጥናቶች እና ምክክሮች ሲደረጉበት እንደቆየ ተጠቁሟል።

ከገለፃው በኋላ ሁለቱ ክለቦች በበላይ ጠባቂዎቻቸው አማካኝነት የስምምነት ፊርማ ያኖሩ ሲሆን የጋራ የባንክ አካውንት ከነገ ጀምሮ ተከፍቶ ስራዎች እንደሚጀመሩ በመጨረሻ ተገልጿል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡