የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወቅታዊ መረጃዎች

የመርሐ ግብር ለውጦች

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች ቀርተውታል። በዚህ ሰዓትም የምድብ ሀ እና ሐ 19ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን የምድብ ለ 18ኛ ሳምንት ላይ ይገኛል። በዚህ ሳምንትም ሁሉንም ምድቦች እኩል ለማስኬድ በማሰብ በርካታ ጨዋታዎች የማይከናወኑ ይሆናል።

የከፍተኛ ሊግ ዋና ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም አህመድ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ምድብ ሀ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ከደሴ ከተማ ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ በ31ኛው ደቂቃ በመቋረጡ እና ደሴ ከተማ በሂሳብ ስሌት የወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደግ እድል ያለው በመሆኑ፤ እንዲሁም በምድብ ሐ ካፋ ቡና ከ ሻሸመኔ የሚደርጉት ተስተካካይ ጨዋታ በወራጅ ቀጠናው ላይ ተፅእኖ ስለሚፈጥር በዚህ ሳምንት መጨረሻ የሚደረጉ ይሆናሉ። በሁለቱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ምክንያትም የምድብ ሀ እና ሐ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የማይከናወኑ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ የምድብ ለ 19ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከተናውነው ከሌሎቹ ምድቦች ጋር በጨዋታ ሳምንት ይስተካከላል።

የምድብ ለ ወሳኝ ጨዋታዎች

ከሌሎች ምድቦች ይልቅ ከፍተኛ ፉክክር እየታየበት በሚገኘው ምድብ ለ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ የሚከናወኑ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ እየተፎካከሩ የሚገኙትን ሦስት ቡድኖች እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

የሠንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ በሜዳው ግርጌ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ፖሊስን ያስተናግዳል። ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው የሚገኘው ነጥብ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ውጥረት የተሞላበት እንደሚሆን ይጠበቃል። በመጀመሪያው ዙር መርሐ ግብር ወልቂጤ ከሜዳው ውጪ ድሬዳዋ ፖሊስን 3-2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ስለ ጨዋታው የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ይህን ብለዋል። “ጨዋታው ከባድ ነው፤ ሁለታችንም ነጥቡን እንፈልገዋለን። ከተጋጣሚያችን ነጥብ ማግኘት አለብን። ምክንያቱም መሪነታችንን ማስቀጠል ስላለብን። ቡድናችን አሁን ላይ በስነ ልቦና ሆነ በቴክኒኩ ከመቼውም በላይ ጥሩ ላይ ነው። የራሳችንን አጨዋወት ለይተን እና ቀርፀን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው። በሜዳችን እንደመሆኑ መጠን ተጭነን የምንጫወት ይሆናል። ከዚህም በኋላ ያለውን ጨዋታ በጥንቃቄ በመጫወት ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ህልማችንን እናሳካለን። ” ብለዋል።

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን የመሪውን ነጥብ መጣል ተስፋ እያደረገ ናሽናል ናሽናል ሴሜንትን ይገጥማል። ጨዋታው እንደ ወልቂጤ ሁሉ ላለመውረድ ከሚፋለም ቡድን ጋር እንደመሆኑ መድን ከናሽናል ጠንካራ ፈተና ይጠብቀዋል። በመጀመሪያው ዙር ናሽናል ሴሜንት 0-0 ኢትዮ መድን መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በጨዋታው ዙርያ የመድኑ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑዕሰገድ እንዲህ ይላሉ። “ጨዋታው ለሁለታችንም ወሳኝ ፤ ነጥቡ ሁለታችንም የሚያጓጓ ነው። እነሱ ላለመውረድ እኛ ደሞ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ስለምንጫወት ከባድ ነው። ሆኖም ቡድኔ በሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። እንደስጋትም ሆነ እንደ መልእክት ማስተላለፍ የምፈልገው አካል አወዳዳሪው አካል ውድድሩን ከሌላው ጊዜ በይበልጥ አትኩሮት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው። ዳኞች በአግባቡ ሊመደቡ ይገባል። ሚዳያዎች በቦታው እና በጊዜው በመገኘት ውድድሩን ለማህበረሰቡ ማድረስ አለባቸው። በእኔ እምነት የሚገባው ቡድን ማለፍ አለበት። ይህ ይሆን ዘንድ ሁላችንም በእውነት መንገድ መሄድ አለብን። ” ብለዋል።

ሌላው የማደግ ተስፋን ሰንቆ እየተፎካከረ የሚገኘውና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢኮስኮ በተመሳሳይ ሰዓት ኦሜድላ ሜዳ ላይ ከሌላው የወራጅ ቀጠና ተፎካካሪ የካ ክ/ከተማ ጋር ይጫወታል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ተገናኝተው ኢኮስኮ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ጨዋታውን አስመልክቶ የኢኮስኮ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እንዲ ይላሉ። ” ጨዋታው ከባድ ነው። ሆኖም ቡድናችን በጥሩ አቋም ላይ ነው። ዓመቱን ሙሉ ማለት ይቻላል ወጥ የሆነ አቋም አሳይቷል። ለተመልካች የሚያስደስት እና እግር ኳስ መዝናኛ መሆኑን ተጫዋቾቼ ሲያሳዩ ቆይተዋል። አሁንም ይህን አጨዋወት ይዘን መቀጠል ነው ምርጫችን። አወዳዳሪው አካል በይበልጥ በዚህ ወቅት ለሁሉም ጨዋታዎች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ” ብለዋል።

የደሴን እጣ ፈንታ የሚወስነው የምድብ ሀ ጨዋታ

የፊታችን እሁድ በምድብ ሀ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ብቻ ይደረጋል። ወልዲያ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ከ ደሴ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀሪ 60 ደቂቃዎች የሚከናወን ሲሆን ደሴ ከተማ ካሸነፈ ከመሪው ሰበታ ከተማ ያለውን ልዩነት ወደ 8 በማጥበብ ጭላንጥል የማደግ ተስፋውን ይዞ የሚቀጥል ይሆናል።

ከሳምንታት በፊት የተደረገው ይህ ጨዋታ 31ኛ ደቂቃ ላይ በደጋፊዎች ረብሻ መቋረጡ የሚታወስ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር መርሀ ግብር ደሴ ላይ 0-0 መለያታቸው የሚታወስ ነው።

ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ አስደናቂ መሻሻል እንዲያሳይ የረዱት የደሴ ከተማው አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ ስለ ጨሳታው ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል። “እግር ኳስ ደስ ከሚለው ባህሪው አንዱ የማይታሰብ ነገር መከሰቱ ነው። ከተጋጣሚያችን ነጥብ ማግኘት አለብን ምክንያቱም ወደ ሻምፒዮናነት መምጣት የምንፈልግ ከሆነ ሁሉንም ጨዋታ ማሸነፍ አለብን። እሳካሁንም ቡድናችን ጨዋታዎቹን ሲያከናውን ለእያንዳንዱ ትልቅ ክብደት በመስጠት ነው። ከተጋጣሚያችን ጋር የደርቢነት ስሜት አለ የአሰልጣኙም ስብስብ በጣም ጥሩ ነው።”

የዚህ ሳምንት ጨዋታዎች

ምድብ ለ (19ኛ ሳምንት)

ቅዳሜ

ወላይታ ሶዶ 9:00 ሀምበሪቾ

እሁድ

ነገሌ አርሲ 9:00 ዲላ ከተማ
ወልቂጤ ከተማ 9:00 ድሬዳዋ ፖሊስ
አዲስ አበባ ከተማ 9:00 ሀላባ ከተማ
ኢትዮጵያ መድን 9:00 ናሽናል ሴሜንት
የካ ክ/ከተማ 9:00 ኢኮስኮ

ምድብ ሀ (ተስተካካይ)

እሁድ

31′ ወሎ ኮምበልቻ 4:00 ደሴ ከተማ (ወልዲያ)

ምድብ ሐ (ተስተካካይ)

እሁድ

ካፋ ቡና 9:00 ሻሸመኔ ከተማ (ጅማ)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡