የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 3-2 ሀዋሳ ከተማ

በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደቡብ ፖሊስ ከመመራት ተነስቶ ሀዋሳን 3-2 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“ዛሬ ደስ ያለኝ በጨዋታው እንቅስቃሴ እንጂ በውጤቱ አይደለም” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ደቡብ ፖሊስ)

ስለ ድሉ

“ከእረፍት በፊት ነበር ጨዋታውን መጨረስ የሚገባን፤ አይታችሁታል። በርካታ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ስተናል። እነሱ ግን ሶስት ጊዜ ነው ግብ ጋር ደርሰው ሁለቱን ተጠቀሙ። ይህ እነሱን ቀዳሚ አደረጋቸው። እነዚህን ስህተቶቻችንን በእረፍት ሰዓት አስተካከልን፤ ትክክለኛ የተጫዋች ለውጥ አድርገን አሻሻልን፡፡ ከእረፍት በኃላ ከዚህ በላይ እናገባ ነበር። ተጫዋቾቻችን ላይ ያለው ጉጉት ውጤት ለማምጣት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ ነው ጎሎች የተሳቱት እንጂ ከዚህ በላይ ግብ አግብተን ማሸነፍ ነበረብን፡፡

“ስለመውረድ አይደለም የማስበው ቡድኑ  እንዲያሸነፍ ነው የኔ ስራ። መውረድ ያለው በማሸነፍ እና በመሸነፍ ስሜት ውስጥ ነው። ቀጣይ የመቐለን ጨዋታ ለማሸነፍ ከዚህ በላይ በተሻለ ተዘጋጅተን እንሄዳለን ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ይሄ ወሳኝ ለኛ ነው። የምንጥለው ነጥብ ሁሉ ዋጋ ስለሚያስከፍለን ተጫዋቾቼ በዚሁ እንደሚቀጥሉ እተማመናለሁ። ዛሬ በጣም ተደስቻለሁ። ደስ ያለኝ በጨዋታው እንቅስቃሴ እንጂ በውጤቱ በተሰማኝ ስሜት አይደለም”

የብርሀኑ እና የተሻ ቅያሪ ያበረከተው አስተዋጽኦ

“ለኔ ሁሉም ተጫዋች ዋጋ ከፍለዋል። ከኃላ ያሉ ተጫዋቾች ለየተሻ ኳሱን ባይሰጡት ኳሱ አይገባም። ቅያሪው የታክቲካል ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ኤርሚያስ ብዙ ወደኋላ ይዘገይ ነበር። ወደፊት የሚሄድ ሰው ስለፈለግን እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። ኤርሚያስ ጨዋታው አንሶት አይደለም። ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾች ግን  ይበልጥ ተነሳሽነት ላይ ነበሩ። መልበሻ ቤት እናሸንፋለን የሚል ተነሳሽነት ውስጥ ነበሩ፡፡ ይሄ ይሄ ደግሞ ለውጥን አምጥቷል። ቅያሪው ብቻውን ሳይሆን የሁሉም እንቅስቃሴ ለዚህ ድል አስተዋፅኦ ነበረው።

“ያላቸውን ኃይል አውጥተው መጠቀማቸው ይህን ውጤት እንዲያመጡ አስችሏቸዋል” አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

“የመጀመሪያው እና ሁለተኛው አጋማሽ ሁለት አይነት መልክ ነበረው፡፡ በእርግጥ የመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ለማጥቃት የነበራቸው ነገር ጥሩ ነበር። ጎል የማግባት አጋጣሚዎችን አግኝተው አልተጠቀሙበትም። እኛ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እየሄድን ግብ ማግባት ችለናል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ግን ሙሉ በሙሉ ተበልጠናል። በኳስ ጨዋታ የምሰራው ስህተት ዋጋ ያስከፍልሀል። እኚህ ደግሞ ለሽንፈታችን ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሁለተኛ አርባ አምስት እንደጀመርን ነበር ግብ የተቆጠረብን። ይሄ ደግሞ በራስ መተማመናችንን አዳክሞ ይሄ ውጤት ሊመጣ ችሏል፡፡ ”

የተጫዋቾች ለስህተት መጋለጥ

“ተጫዋች ስህተት ይሰራል። እኛ ስህተት ልንፈጥር የቻልነው ምናልባት የነሱ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ተጭነው መጫወታቸው ነው። ስህተቱን የፈጠረው የመጨረሻ ተከላካይ ነው። በተለይ ሁለቱ ጎል ላይ። እነሱ ያላቸውን ኃይል አውጥተው መጠቀማቸው ይህን ውጤት እንዲያመጡ አስችሏቸዋል፡፡  ያላቸውን አማራጭ በደንብ ተጠቅመዋል። ከእረፍት በኋላ መጫን ፈለጉ፤ ሲጫኑን ያልጠበቅነው ነገር ተከስቷል፡፡ ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡