ሀዋሳ ከተማ የሴቶች ጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን ሆነ

የ2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ፍፃሜውን ሲያገኝ ሀዋሳ ከተማ እና ንግድ ባንክ በመደበኛው ደቂቃ 1-1 ተለያይተው በተሰጠው የመለያ ምት ሀዋሳ ከተማ 4-3 በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ ቻምፒዮን ሆኗል፡፡

ሀዋሳ ከተማ መከላከያን፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ጌዲኦ ዲላን በማሸነፍ የዛሬው የፍፃሜ ተፈላሚዎች ነበሩ፡፡ የክብር እንግዶቹ እስኪመጡ ከተያዘለት ደቂቃ ሀያ ያህል ዘግይቶ የጀመረው ይህ ጨዋታ የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ስራ-አስኪያጅ አቶ ጠሀ አህመድ የእለቱ እንግዳ ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን በወቅቱ ባለመገኘታቸው ከሌሎች የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች በመሆን ጨዋታውን አስጀምረውታል፡፡

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ፀሀይ መሪነት የተጀመረው ይህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ 30 ያህል ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች በይበልጥ በመፍጠር በተለይ ከግራ መስመር ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ አጥቂዋ መሳይ ተመስገን በመጣል፤ ንግድ ባንኮች ከቅብብል በሚገኙ ዕድሎች ወደ ሽታዬ እና ረሂማ በማድረስ ላይ አተኩረው ታይተዋል፡፡ ገና በጊዜ የባንክን የተከላካይ ክፍል ስታስጨንቅ የነበረችሁ መሳይ ተመስገን በግራ በኩል ብዙነሽ ሲሳዬን አልፋ 6ኛው ደቂቃ በቀጥታ የመታችውን ኳስ ንግስቲ መዓዛ በፍጥነት የተቆጣጠረቻት ቅድሚያውን የምትወስድ ሙከራ ነበረች። 17ኛው ደቂቃ ዓይናለም በቀኝ በኩል ክልሉ ወደ ባንክ የመከላከል ክፍል የላከችውን ኳስን መሳይ ተመስገን ለማግኘት ስትሞክር ንግስቲ ቀድማ ይዛባታለች፡፡

ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ኳስን ይዘው በተለይ በቀኝ አቅጣጫ በሽታዬ አማካኝነት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ባንኮች በቀላሉ ጠጣር አደራደርን ያየንበት የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ሊገቡ ግን አልቻሉም። ይሁንና 20ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ብልጠቷን ተጠቅማ የሀዋሳዋን ግብ ጠባቂ መውጣት አይታ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ ዓባይነሽ እንደምንም ወደ ኃላ ተስባ ያወጣችባት ኳስ አስቆጪ ነበረች። 28ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ የተሰጠውን ቅጣት ምት ገነሜ ወርቁ አክርራ መታ የግቡ ብረት የመለሰውም ባንክን መሪ የሚያደርግ ዕድል ነበረች፡፡

37ኛው ደቂቃ ነፃነት መና ከአጋማሽ መሬት ለመሬት ያሳለፈችላትን ኳስ መሳይ ተመስገን ሶስት የባንክ ተከላካዮችን እንዲሁም ግብ ጠባቂዋን ንግስቲን አልፋ በማስቆጠር ሀዋሳን መሪ አድርጋለች። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ አጥቂዋ ነፃነት መና ክፍት የማግባት አጋጣሚን አግኝታ ጥሩአንቺ በኃላ ደርሳ አስጥላት በ1-0 ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በጣለው ከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ ሀዋሳዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ብለው የገቡ ሲሆን በአንፃሩ ንግድ ባንኮች ግን በሀዋሳ ላይ ብልጫን መውሰድ ችለዋል፡፡ ሽታዬ ሲሳይ በግራ በኩል የግል ጥረቷን ተጠቅማ ወደ ግብ ስትልክ ረሂማ በግንባር ገጭታ ለጥቂት የወጣባት፣ ከቅጣት ምት ህይወት ደንጊሶ በረጅሙ ወደ ግብ መታ ዓባይነሽ የመለሠችባት ባንኮች ብልጫ ለማሳየታቸው የሚጠቀሱ ሲሆኑ 64ኛው ደቂቃ ብርቱካን ገብረክርስቶስ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ህይወት ደንጊሶ ከሳጥን ውጪ አክርራ በመምታት መረብ ላዬ አሳርፋ ንግድ ባንክን 1-1 እንዲሆን አስችላለች ፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ወደ መጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ የተመለሱት ሀዋሳዎች ቢሆኑም መሪ የሚያደርጋቸውን ግብ ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡ በተለይ መሳይ ከማዕዘን አሻምታ ትዝታ ኃይለሚካኤል በግንባር ገጭታ ንግስቲ የያዘችባት ተጠቃሽ ነች። ሀዋሳ ከተማዎች አቻ መለያየታቸውን በመረዳት ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው ግብ ጠባቂዋ ዓባይነሽን በማስወጣት ትዕግስት አበራን ተክተው ካስገቡ በኃላ 1-1 ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ወደ መለያ ምት ባመራው ፍልሚያም ሀዋሳ ከተማ ከተሰጡት አምስት ምቶች መሳይ ተመስገን ከማምከኗ ውጪ አራቱን ሲያስቆጥሩ ንግድ ባንኮች ከአምስቱ ሶስት አስቆጥረው ብርቱካን ገብረክርስቶስ ወደ ውጪ መታ ስታወጣ የባንክ የመጨረሻ መቺ የነበረችው ታሪኳ ዴቢሶ ተቀይራ በገባችው ትዕግስት አበራ ተመልሶባት በሀዋሳ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳም 2009 ላይ ደደቢት አሸንፎ ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ ይህን ውድድር አሸናፊነት ለሁለተኛ ጊዜ ያሳካ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሶፊያ አልማማው ሻምፒዮን ለሆነው ለሀዋሳ ከተማ ቡድን ዋንጫ አበርክተው ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡