በዳኞቻችን ዓለምአቀፍ ውድድሮች ቆይታ ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በተከናወነው የ2019 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ላይ በዋና ዳኝነት የተሳተፈችው ሊዲያ ታፈሰ እንዲሁም ዓርብ በተጠናቀቀው የ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በዋና እና በረዳት ዳኝነት የተሳተፉት በዓምላክ ተሰማ እና ተመስገን ሳሙኤል ስለነበራቸው ቆይታ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ከተገኙት ሦስቱ ዳኞች በተጨማሪም የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በቦታው ተገኝተው ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

መግለጫውን የጀመሩት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ዳኞቹ ሃገርን ወክለው ስለሰሩት ስራ ምስጋና አቅርበው ንግግራቸውን ጀምረዋል።” በመጀመሪያ ሃገርን ወክለው በኢንተርናሽናል ደረጃ ስራዎችን ሰርተው ለመጡት ዳኞቻችን ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውስጥ የነበረ ችግር አለ። ይህም ደግሞ ሰዎች ትላልቅ ስራዎችን ሰርተው ሲመጡ በአግባቡ አመስግነን እውቅና አንሰጣቸውም። ይህንን ነገር ግን ለማሻሻል እየሰራን ነው። ዳኞቻችን ሃገርን ወክለው እንደመሄዳቸው ክብር ይገባቸዋል። ስለዚህ ዓመታዊ ውድድራችንን ከቋጨን በኋላ በምናደርገው ዝግጅት ላይ ዳኞቻችን በሚገባ እውቅና እንሰጣለን።” በማለት ተናግረዋል።

ከአቶ ዮሴፍ ቀጥሎ በፈረንሳዩ የሴቶች ዓለም ዋንጫ አንድ ጨዋታ (ስኮትላንድ ከጃፓን) የመራችው ሊዲያ ታፈሰ ስለነበራት ቆይታ ሃሳቧን አካፍላለች።” እውነት ለመነገር በፈረንሳይ የነበረኝ ቆይታ ቀላል የሚባል አልነበረም። በብዙ ነገሮች ተፈትኜበታለው። ነገር ግን ከውድድሩ ክብደት አንፃር ጠንካራ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚገባኝ አምኜ በደንብ ተዘጋጅቼ በጥሩ ሁኔታ ጨዋታ መርቻለው። የሆነው ሆኖ ያሉትን ነገሮች የሚፈትኑ ቢሆኑም እነዛን ነገሮች ተቋቁሜ መጥቻለው” በማለት ቆይታዋን በአጭሩ አስረድታለች።

ከሊዲያ በመቀጠል መድረኩን ያገኘው በዓምላክ ተሰማ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምስጋና አቅርቦ እንዴት እዚህ እንደደረሰ አስረድቷል። “በመጀመሪያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከሚዲያው ጋር እንድንገናኝ ስላደረገን አመሰግናለው። እዚህ አፍሪካ ዋንጫ ላይ እንድሳተፍ ያደረገኝ በ2013 የነበረብኝ ቁጭት ነው። በዛን ጊዜ የወንድ ብሄራዊ ቡድናችን በአፍሪካ ዋንጫው ሲሳተፍ እኔ አልሄድኩም ነበር። ከዛን ጊዜ አንስቶ ግን ትልቅ ቁጭት በውስጤ ስለነበር ተግቼ ሰርቼ ለዚህ በቅቻለው”። በማለት ሃሳቡን ቀጥሏል።

” በግብፅ የነበረን ቆይታ በጣም ጥሩ ነበረ። ጥሩ ልምድ አካብቼበታለው። በአጠቃላይ በመሃል ዳኝነት የመራሁዋቸው ጨዋታዎች አራት ናቸው። በጠቅላላ ግን ጥሩ ቆይታ ነበረኝ” ብሏል።

ከበዓምላክ ጋር አብሮ ወደ ግብፅ በመጓዝ አንድ ጨዋታ በረዳት ዳኝነት የመራው ተመስገን ሳሙኤል እንደነ ሊዲያ እና ባምላክ ሁሉ ስለነበረው ቆይታ በአጭሩ ተናግሯል። ተመስገን በንግግሩ በህይወት ዘመኑ አግኝቶት የማያውቀውን ዕድል በአፍሪካ ዋንጫው እንዳገኘ በመግለፅ ለወደፊቱ የዳኝነት ቆይታው ጥሩ ጥሩ ግብዓቶችን እናዳገኘና ከትልልቅ የአፍሪካ ዳኞች ትምህርቶችን እንደወሰደ አስረድቷል።

ከዳኞቹ ገለፃ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች ከብዙሃን መገናኛዎች የተሰነዘረ ሲሆን በተለይ በዓምላክ በአፍሪካ ዋንጫው የፍፃሜ ጨዋታ ይመራል ተብሎ ተሰራጭቶ ስለነበረው ዜና ማብራሪያ ሰጥቷል።” ባለፈው ሳምንት የወጣው ዜና የተሳሳተ ነበር። ይህ ደግሞ የመጣው ከውጪ ሀገር ሚዲያዎች ነው። ለምን እንደሆነ አላውቅም ግን ይህ የተሳሳተ ዜና ከውጪ ሃገር ሚዲያዎች እንደመጣ አረጋግጫለው። ይህ ጉዳይ ደግሞ በካፍ የዳኞች ምደባ ኮሚቴዎች ላይ የተወሰነ ጫና እንዳሳረፈ ተረድቻለው። ነገር ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። ለቀጣይ ግን ቃል የምገባላችሁ በቀጣዩ አፍሪካ ዋንጫ ተግቼ ሰርቼ የፍፃሜ ጨዋታ እንደምዳኝ ነው።” በማለት ስለ ጉዳዩ ሃሳቡን ሰጥቷል።

በመጨረሻ በዓምላክ የአፍሪካን ውድድሮች ከሚመራ እና የሃገር ውስጥ ውድድሮች ከሚመራ ተብሎ ለተነሳለት ጥያቄ ምርጫው የሃገር ውስጥ ጨዋታዎችን በተለይ የደርቢ ጨዋታዎችን መምራት ፍላጎቱ እንደሆነ አስረድቶ ሃሳቡን ቋጭቷል።

በመግለጫው መዝጊያ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ዳኞች በሃገር ውስጥ ውድድሮች ጫና እየተደረገባቸው እንደሚዳኙ ነገር ግን ከነዛ ጫናዎች ነፃ ሆነው ቢዳኙ ስኬታማ እንደሚሆኑ ተናግረው መግለጫው ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: