ቻን 2020 | ዋልያዎቹን በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በአምበልነት የሚመራው ተጫዋች ታውቋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን የማጣርያ ውድድር ዝግጅቱን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በማከናወን ላይ ይገኛል። አስቻለው ታመነን የቡድኑ አምበል አድርጎም መርጧል።

ወደ ጅቡቲ አቅንቶ የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድኑ በአዳማ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ እያደረገ የቆየ ሲሆን ከትላንት ጀምሮ በቀን ወደ አንድ ዝቅ በማድረግ ዝግጅቱን ቀጥሏል። በስብስቡ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል በብሔራዊ ቡድን የተሻለ ልምድ ያለው የሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋቹ አስቻለው ታመነ በማጣርያ ጨዋታዎቹ ላይ አምበል ሆኖ እንዲመራ የተመረጠ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን አጋሩ ሙሉዓለም መስፍን ሁለተኛ አምበል ሆኖ መሾሙ ታውቋል። ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው ያለፉት አራት የነጥብ ጨዋታዎችን ጌታነህ ከበደ (3) እና ሽመልስ በቀለ (1) በአምበልነት መምራታቸው ይታወሳል።

በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ዙርያ ዛሬ በጁፒተር ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ የተገኘው አስቻለው ታመነ ስለ ማጣርያው በሰጠው አስተያየት ተጋጣሚያቸውን እንደማይንቁ ገልጿል። ” ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው። ሁሉም ተጨዋቾች ጋር ያለው ነገር ደስ ይላል። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ጋር እንደሚወራው ተጋጣሚያችንን አንንቅም። ምክንያቱም ውድድሩ ለእኛ በጣም ያስፈልገናል። በትልቅ መድረክ ከተሳተፍን ጊዜያት እየተቆጠሩ ስለመጡ በውድድሩ መሳተፍ እንፈልጋለን። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ጂቡቲን ማሸነፍ አለብን። በአጠቃላይ ለተጋጣሚያችን ትኩረት ሰጥተን ብንዘጋጅም የተለየ ዝግጅት ግን አናደርግም።” በማለት ሃሳቡን አካፍሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡