የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 2-0 ጅማ አባ ጅፋር

በዛሬው ዕለት ጅማሮውን ያደረገው የአዳማ ከተማ ዋንጫ ባለ ሜዳው አዳማ ከተማ በሱሌይማን ሰሚድ እና ኃይሌ እሸቱ ጎሎች ጅማ አባ ጅፋን 2-0 አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


“በእንቅስቃሴው ቡድናችን ዛሬ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አድርጓል” አስቻለው ኃይለሚካኤል

የጨዋታው እንቅስቃሴ

በዝግጅት ስለቆየን ተጫዋቾቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ እንዲህ ያሉ ውድድሮች መዘጋጀታቸው መልካም ነው። በእንቅስቃሴው ቡድናችን ዛሬ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አድርጓል።

ያገኟቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀም

ይህ ችግር እንዳለ ነው። በሀገር ደረጃም መሠረታዊ ችግር ሆኖ እየታየ ያለው ያገኙትን አጋጣሚ ያለ መጠቀም ነው። በቀጣይ በምናደርጋቸው ጨዋታ እና በልምምዶቻችን ስህተቶቻችንን በማረም የአጨራረስ ችግሮቻችንን እንቀርፋለን።

“ኳሱን ይዞ የሚጫወት ቡድን ለመስራት ጥረት እያደረግኩ ነው” ዻውሎስ ጌታቸው

የቡድኑ እንቅስቃሴ

እንዳያችሁት ወጥ የሆነ ኳሱን ይዞ የሚጫወት ቡድን ለመስራት ጥረት እያደረኩ ነው። በዛሬውም ጨዋታ ይህን ለማሳየት ጥረት አድርገናል። ምንም እንኳ ውጤቱ ጥሩ ባይሆንም። በቀጣይም ያሉኝን ተጫዋቾች ተጠቅሜ የጅማ ህዝብ የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት ጠንክሬ እሰራለው።

የቡድኑ ተጫዋቾች አለመሟላት

የማዘጋጀው 25 ተጫዋቾች ነው። በእርግጥ ቡድኑን ሚዛናዊ የሚያደርጉ ጥሩ ተጫዋቾች ዛሬ እንዳልገቡ ግልፅ እና ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ስለዚህ እኔ ሁልጊዜ መዘጋጀት እንዳለብኝ አስባለው። ብዙ ሩጠው ያልጠገቡ ወጣት ተጫዋቾች ያሉበት ቡድን በመሆኑ ከዚህ ውድድር ውጭ ተከታታይ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ጠንካራ ቡድን ለመስራት እየተዘጋጀሁ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ