አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ዙርያ መግለጫ ሰጥተዋል

የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያን አስመልክቶ ዛሬ ከሰዓት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።

በይዘቱ አጠር ያለ በነበረው መግለጫው አሰልጣኝ ብርሃኑ በቅድመ ማጣርያው ከጅቡቲ ጋር ስለሚጠብቃቸው ጨዋታና በሴካፋ ውድድር ስለነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ስለ መጪው የጅቡቲ ጨዋታ

” የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ባለፋት 18 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ላይ ከአንዴም ሦስት ጊዜ የመሳትፍ እድሉን ማግኘት ችለናል። ባለፈው ለሴካፋው ውድድር ባጠረ ጊዜ ውስጥ ዝግጅት አድርገን ተሳትፈን መመለስ ችለናል። ከዚያም መልስ ፌደሬሽኑ ጠይቆኝ ባይሆንም በግሌ በአፋጣኝ በውድድሩ ላይ ስለነበረን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚገልፅ ሪፖርት ለፌዴሬሽኑ አቅርቢያለሁ። በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከጅቡቲ ጋር መደልደላችን እድለኛ ያረገናል፤ ነገርግን እኛ እንደሙያተኛ ነገሮችን አቅልለን መመልከት አይገባንም። የእኛ ድርሻ አሁን ላይ ብቻ በማሰብ መገደብ የለበትም ቡድኑን መገንባትና በሂደት የተሻለ ነገር ለማስመዝገብ መስራት ይኖርብናል። በነገራችን ላይ የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ላለፉት 5 ዓመታት አብረው የቆዩ ናቸው በሒደት ሌሎች ትውልደ ጅቡቲ ተጫዋቾችን በመጨመር አሰልጣኟ ጠንካራ ሥራ እየሰራች ትገኛለች። ስለዚህ በሚባለው ልክ ደካማ ቡድን አይደለም።

“የአፍሪካ ዋንጫ ከሴካፋ በብዙ መመዘኛዎች የተለየ ነው ፤ ለመዘጋጀት በቂ የሆነ ጊዜ አለን ፣ የሊጉ ክለቦች ውድድር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ በተጨማሪም ከ17ና 20 በታች ብሔራዊ ቡድኖች በውድድር ላይ መሆናቸው ለእኛ የተሻለ አጋጣሚን ይፈጥርልናል። ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ ሾልከው የገቡ ተጫዋቾች እንኳን ቢኖሩ አሁን ላይ ለማጥራት እድል ይሰጠናል።

” አሁን በንፅፅር አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቀለል ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ እንደመገኘታችን ውጤት ማምጣት ካልቻልኩ ችግሩ ከእኔ ሊሆን ይችላል።

“ይህ የማጣሪያ ውድድር ቃል የገባንበት ስለሆነ ማሳበብ ከእኛ አይጠብቅንም ፤ ከእኛ የሚጠበቀው ጠንክረን በመስራት ሀገራችን ከፍ ለማድረግ መስራት ብቻ ነው።”

ስለሴካፋው ውድድር ድክመቶች

“በሴካፋው ውድድር ወቅት ትልቁ ችግር የነበረው ቡድኑ የተገነባው በ10 ቀን ውስጥ መሆኑ ነው። ከነበረው የዝግጅት ጊዜ ማነስ የተነሳ ከዚህ ቀደም የማውቃቸው ተጫዋቾች ላይ ለማተኮር ተገድጃለሁ። ሁለተኛው ችግር የነበረው የክለብ ተጫዋቾች ቅድመ ዝግጅት የጀመሩበት ጊዜ ከብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ጋር ተቀራራቢ መሆኑ ነበር። በተጨማሪም በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ የአየር ንብረት አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ አልቻልንም። ይህም በውድድሩ ወቅት ከፍተኛ የጨዋታ ዝግጁነት ችግር እንዲኖርብን አስችሏል። ሌላውና ዋነኛ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች መቀያየር አሰልጣኞች እቅድ ይዘው እንዳይሰሩ ያደርጋል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ