መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፬) | ቅንጭብጫቢ ትውስታዎች ለፈገግታ

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቆይታ እና ከተክሌ ኪዳኔ ጋር ስለተፈጠረው ክስተት ባለፉት ሳምንታት አጫውተናችኋል። ዛሬ ደግሞ ለፈገግታም ዘመንን ለማነፃፀርም በማለት የታላቁን እግርኳሰኛ ቅንጭብ ገጠመኞች እናነሳለን።

ማስታወሻ ፡ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ገነነ ሊብሮ ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እና ልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ የታላቁን ሰው ህልፈት ተከትሎ በተከታታይ ያወጣቸው ፅሀፎች ዋነኛ ግብዓት እንደሆኑን እንገልፃለን።

ታላቁን የእግኳስ ሰው መዘከር በጀመርንበት የመጀመሪያው ፅሁፋችን ተማሪ እያለ በክረምት ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ወደ ጎንደር መሄድ ሲገባው ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትሎ ወደ ድሬዳዋ ማቅናቱን እና ከድሬዳዋ ኮተን ጋርም የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረጉን አንስተን ነበር። በዚህ ጨዋታ ላይ የተፈጠረ ፈገግ የሚስብለውን አጋጣሚ ደግሞ ለዛሬ መርጠነዋል። መንግሥቱ ድሬዳዋ ኮተን ጨዋታውን 3-1 እየመራ በነበረበት ወቅት ከእሱ ጋር ቡድኑን የተቀላቀለው እና በጨዋታው ላይ የተጎዳው ዑመር ሮያሌን በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገባው። መንግሥቱ እስከዛ ጊዜ ድረስ በባዶ እግር እንጂ ታኬታ አድርጎ ተጫውቶ አያውቅም። በጣም ጓጉቶ ስለነበርም ሮጦ ወደ ጨዋታው ሊገባ ሲል ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ የፌዴሬሽኑ ህግ አስገዳጅም ስለነበር ‘ታኬታ መጫማት አለበት’ አሉ። የነበረው አማራጭ አንድ ብቻ ነበር ፤ በሌላ ሰው ታኬታ መጫወት። በወቅቱ አቶ ፀሀዬ የተባሉ ዕድሜያቸው በመግፋቱ ለጨዋታ ባይሆኑም ለኳስ እና ለቡድኑ ልዩ ፍቅር የነበራቸው ሰው የጋሽ ይድነቃቸው በዛ ዕድሜ መጫወትንም በማየት ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጠው ነበር። የዑመርን መጎዳትም ሲያዩ ወደ ሜዳ ገብተው ለመጫወት መጓጓታቸው አልቀረም። ሆኖም ያደረጉትን አዲስ ታኬታ በእሳቸው ጉጉት ተተክቶ ለሚገባው ታዳጊው መንግሥቱ እንዲሰጡት ሲጠየቁ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። ከቡዙ ማግባባት በኋላ ግን ጫማቸውን ሰጥተው በባዶ እግር ለመቀመጥ ተገደዱ። ታዳጊውም አላሳፈራቸውም ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑን ባለድል አደረገ። አቶ ፀሀዬም በዚህ ተደስተው አዲሱን ጫማ ለመንግሥቱ በስጦታነት አበተከቱለት። ያ ጫማም ለአዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክስተት ክከድሬዳዋ መልስ ቡድኑ ወደ ናዝሬት ተጉዞ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ብዙ ግብ እንዲያስቆጥር እና ስሞ በፍጥነት ከፍ ብሎ እንዲታወቅ አስችሎታል።

ይህ ጨዋታ መንግሥቱ ወርቁ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታኬታ ጋር ተዋውቆ የተሰለፈበት እና የመጀመሪያውን ሦስታ የሰራበት ብቻም ሳይሆን የመጀመሪያውን ከባድጉዳት ያስተናገደበትም ነበር። አጋጣሚውን አይረሴ የሚያደርገው ደግሞ ጉዳት የደረሰበት በተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ሳይሆን በጋሽ ይድነቃቸው አማካኝነት መሆኑ ነው። በጨዋታው ሁለት ግብ አስቆጥሮ ውጤቱ 3-3 ከሆነ በኋላ ለራሱ ሦስተኛውን ለቡድኑ ደግሞ አራተኛውን ግብ ሲያስቆጥር የገጠውን ይህን ክስተት መንግሥቱ ከሊብሮ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ እንዲህ ተርኮት ነበር። ” ጋሽ ይድነቃቸው ጠራኝና ‘ወደ መሀል ግባ’ አለኝ። እኔም እንዳለኝ እየገባሁ መጣሁ። ሰዓት ሲያልቅ ዳኛው ፊሽካ ሊነፋ ሲል ከክንፍ አካባቢ ክሮስ ከተደረገ ኳስ ከኋላቸው ሳያዩኝ ተሽሎክልኬ ሄጄ ጋሽ ይድነቃቸው ኳሱን ከማዕዘን እንደመጣ ለመምታት አነጣጥሮ ስለነበር ተንደርድሮ እግሩን በኃይል ሲሰነዝር እኔ ከኋላው መጥቼ ስመታው በዚያው ጋሽ ይድነቃቸው ኳሱን ያገኘ መስሎት ሲጠልዘኝ እኔ ኳሱን መትቼ ሲገባ ጋሽ ይድነቃቸው እኔን መትቶ ጎል አገባ።” ከጎሉ እንጨት ጋር ተላትሞ ከካሷ ጋር መረብ ውስጥ የገባው መንግሥቱ በወቅቱ ራሱን መሳቱን እናተሸክመው እንደወሰዱት እንዲሁም በእግርኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባድ አደጋ የገጠመው በዚህ ወቅት ስለመሆኑ ለገነነ ጨምሮ አብራርቶለታል።

ቀጣዩ ታሪክ ደግሞ መንግሥቱ በደጋፊው ዘንድ የነበረው ተወዳጅነት ምን ያህል እንደሆነ ከማሳየትም በተጨማሪ በዘመናችን እንኳን የማናስተውለው በዚያ ጊዜ ግን ተጨዋቾች ምንም ያህል ትልቅ ቢሆኑ እንኳን ከቅጣት እንደማያመልጡ የሚያሳይ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። በወቅቱ መንግሥቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ቡድኑም ቁልፍ ተጫዋች የነበረበት እና ስሙ የገነነበት ጊዜ ነበር። ሆኖም ከክለብ እግርኳስ ጎን ለጎን በግሉ በንግድ ላይ ተሰማርቶም ኑሮውን ይገፋ ስለነበር ልምምድ የማያሟላባቸው ወቅቶች ይኖሩ ጀመር። በዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ይሰለጥን በነበረው ቡድን ውስጥ ራሱ መንግሥቱ ጠቁሞ ያስመጣቸው የኮሚቴ አባላት ግን ሦስት ልምምዶች ላይ በመቅረቱ ለሁለተኛው ቡድን እንዲጫወት ወሰኑ። በመሆኑም ዋናው ቡድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን እያደረገ የወቅቱ ትልቅ ተጫዋች እና የብሔራዊ ቡድኑ አጥቂ ግን ከሁለተኛ ቡድኑ ጋር በጃንሜዳ ፣ ኬተቤ እና አባሲዮን ሜዳዎች እየተጫወተ ይገኝ ነበር። ኃላፊዎቹም ከመቅጣት እሱም ቅጣቱን ተቀብሎ በመተግበር ለሁለተኛው ቡድን እንደለመደው ግቦቹን ከማስቆጠር ወደ ኋላ አላሉም። ስምንት ቁጥራቸውን አጥብቀው የሚወዱት ደጋፊዎች በተለይም የመርካቶዎቹ ደጋፊዎች ግን ጨዋታዎቹን እየሄዱ ከመከታተል እና ቅጣቱ እንዲነሳለት ኮሚቴው ላይ ጫና ከማሳደር አልቦዘኑም። በመጨረሻም አሸናፊ ሆኖው የቅጣቱ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት አጥቂያቸውን ወደ ዋናው ቡድን መልሰውታል። ዛሬ ላይ በአንድ የብሔራዊ ቡድን ቁልፍ ተጫዋች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ቢወሰን ውጤቱ ምን ይሆን ነበር ?

መንግሥቱ እንደትልቅ አጥቂነቱ የወቅቱ የተከላካዮች ዋነኛ ትኩረት ነበር። ዱላ ቻይነቱ እየረዳው ተቋቁሟቸው ግቦችን ማስቆጠሩን ባይተውም እነሱም ከኳስ ውጪም ሆነ ከኳስ ጋር እሱን መጎሸም ዋነኛው ቡድናቸውን የሚከላከሉበት መንገድ ነበር። ታድያ መንግስቱም አጋጣሚውን ካገኘ ድፍረት በተሞላበት ብልጠቱ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ የሚያገባበትን መንገድ እነሱን ለማብሸቂያ እና ለመበቀያነት ይጠቀምበትት ነበር። በአንድ ወቅት ከድሬዳዋ ኮተን ጋር በነበረው ጨዋታ ያደረገውን ፈገግ የሚያስብል ድርጊትም እሱ ራሱ ለሊብሮ እንዲህ ተርኮለት ነበር። “አንድ አልታየ የተባለ የመቻል ተጫዋች ነበር። ይሄ ልጅ ሰውነቱ በጣም ግዙፍ ስለሆነ ካገኘህ ጠራርጎ ነው የሚጥልህ። መቻል እያለ ያስቸግረኝ ነበና ከመቻል ወጥቶ ድሬዳዋ ኮተን ገባ። ያጋጣሚ እኛና ኮተን ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና ተገናኘን ከመሀል የተጣለ ኳስ አገኘውና በረኛውን አልፌ ወደ ጎሉ ሄድኩ። እኔና ይሄ ልጅ በጣም እንራራቃለን ኳሷን እየገፋው ብለቃት አይደርስባትም። ግን ምን ሊያደርግ እንደሚከተለኝ አልገባኝም። በኋላ መስመሩ ጋር ስደርስ ቆምኩና ጠበኩት። እሱ ከዛ እየተንደረደረ ሲመጣ ጠብቄው ወደ ሌላ ቦታ የምነዳት አስመስዬ ኳሷን ጥያት ሄድኩ። የዚህን ጊዜ እሱ እየተንደረደረ መጥቶ እኔን እና ኳሷን ጠራርጎ ሊጥለን ሲመጣ እኔን አጣኝ እና ኳሷን ከነኖራው ጠራርጎ መረቡ ውስጥ አስገብቶ አቧራ አቧራ ሆኖ እርሱ ራሱ ተሸፈነ። እኔም ጎሉ ዳር ቆሜ እያጨበጨብኩ ብራቮ የእኛ ጎል አግቢ በዚሁ ከቀጠልክ ኮከብ ግብ አግቢ ትሆናለህ ብዬ ጥዬው ሄድኩኝ። ”

መንግሥቱ የግል ፀባዩ ቁጡ እና በቶሎ የሚበሳጭ ዓይነት መሆኑን ይናገራል። እርግጥ ነው ይህ ፀባዩ ሜዳ ላይ እልኸኛ እና ታጋይ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ ረገድ ፀባዩ ተጋጣሚዎቹ ላይ የበላይነትን ለማሳየት የሚገፋውም ይመስላል። የሚገርመው ግን የዚህ ባህሪው ኃይለኝነት ለተፎካካሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለራሱ የቡድን አጋሮቹም ላይ የሚገለፅ መሆኑ ነው። ሊያውም እንደ ጋሽ ይድነቃቸው ላለ ወደ እግርኳስ እንዲመጣ መንገድ የከፈተለትን እና እጅግ የሚያከብረው ዓይነት ሰው ላይ ሊያውም በሜዳ ውስጥ በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ ሲገለፅ ማየት ትኩረት ይስባል። አጋጣሚው የተፈጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአንበሳ ጋር እየተጫወተ በነበረበት እና ሁለቱ የክለቡ ትታላላቅ ባለገድሎች ሜዳ ውስጥ አብረው በሚሰለፉበት ወቅት ነበር። በጨዋታው መንግሥቱ አብዶ ወደመስራቱ አደላና ኳስ ሳያቀብል በመቅረቱ የጋሽ ይድነቃቸውን ቁጣ ይቀምሳል። ኃይለ ቃል የተቀላቀለበት የጋሽ ይድነቃቸው ወቀሳም መንግሥቱን ቦግ ያደርገዋል። በንዴትም ጨዋታው ላይ ያለውን ሚና ያወርደዋል። በዛ ቅፅበት የተፈጠረውን መንግሥቱ እንዲህ ገልፆት በልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ” ኳስ አጠገቤ ስትመጣ እንኳን መንካት ተውኩ። በዚህ መሀል ላይ ተጋጣሚያችን የአንበሳ ቡድን ግብ አስቆጠረብን። ‘አሁን ደስ አለህ አይደል ?’ አለኝ። እኔም ብስጭት ላይ ስለነበርኩ ‘አዎ’ ብዬ መለስኩለት። በጣም ስለተናደደ እና እጅግ ስለተበሳጨ ሜዳ ውስጥ እኔን ማባረር ጀመረ። እንደምን ብዬ አመለጥኩት። ጋሽ ይድነቃቸው ስለእያንዳንዱ ተጫዋች ባህሪ ያውቃል ፤ ግጥምም ማውጣት ይችልበታል። የእኔንም ባህሪ እና ፀባይ ገምግሞ እንዲህ በማለት ገጥሞልኛል።

በቴክኒክ አይቻል እንዲሁም በግፊያ
እግዚአብሄር አያድርስ የመንግሥቱን ኩርፊያ

በቀጣይ ሳምንት የታላቁን ስምንት ቁጥር የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ