የስታዲየሞች ግምገማ ዛሬ ተጠናቀቀ

በተዋቀረ ሦስት ኮሚቴዎች አማካኝነት በየሀገሪቱ በተመረጡ ስታዲየሞች እና መሠረተ ልማቶች ዙሪያ ሲደረግ የነበረው ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሌሎች አካላትንም በአባልነት አካቶ በተዋቀሩ ሦስት ኮሚቴዎች አማካኝነት ውድድሮች በድጋሚ እንዲጀምሩ እና በተመረጡ ሜዳዎች ውድድሮች እንዲደረጉ ቅድመ ግምገማ ላለፉት ስምንት ቀናት ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ኮሚቴዎቹ ተዟዙረው አስራ ሰባት ሜዳዎች እንደሚገመግሙ ቀደም ተብሎ የተገለፀ ቢሆንም ሦስት ሜዳዎችን ለጊዜው ሳይመለከቱ ቀርተዋል፡፡ የወንጂ ስታዲየም በአካባቢው በተፈጠረ የጎርፍ አደጋ መንገድ ባለመኖሩ፣ የነቀምት ሜዳ መንገዱ ምቹ መሆን ባለመቻሉ እና የመቐለ ስታዲየም ባለው ወቅታዊ የኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ወደ ከተማው ለመጓዝ የ15 ቀናት የለይቶ ማቆያ ቆይታ ስለሚኖረው ወደ ሌላ ጊዜ ቢዞርም ከሰሞኑ መመልከት ያልቻሏቸው ሜዳዎች ሆነዋል፡፡

የተገመገሙ ሜዳዎች ሪፖርት ለሚመለከተው አካል ከነገ ጀምሮ የሚቀርብ ሲሆን ለውድድር ብቁ ናቸው የተባሉም ይፋ በቅርቡ እንደሚደረጉ የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!