በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የወልዋሎ ጨዋታ 2-2 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥብ ከተጋሩበት የመጨረሻ ጨዋታቸው ከተጠቀመበት ስብስቡ ዘላለም አበበ እና ናትናኤል ዳንኤልን አሳርፈው ቢንያም ካሳሁን እና አዲስ ግደይን ተክተው ለጨዋታው ሲቀርቡ ወልዋሎ ዓ.ዩ በአንፃሩ አቻ ከወጡበት የመጀመሪያ ተመራጮች ቡልቻ ሹራን በፉሃድ አዚዝ ለውጠው ገብተዋል።
የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ ፊሽካቸውን በማሰማት ካስጀመሩበት ደቂቃ አንስቶ ጨዋታው የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል እያስመለከተን እስከ ውሃ እረፍት ድረስ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ለጎል የቀረበ ሙከራ መመልከት አልተቻለም ነበር። ከውሃ ዕረፍት መልስ ምንም እንኳን ሙከራዎችን ለማድረግ ይቸገሩ እንጂ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው አደጋ ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ክፍት ቦታ ፍለጋ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።
ብልጫ ቢወሰድባቸውም ኳስን ሲያጡ ወደ ራሳቸው ሜዳ በመግባት በሚሻገሩ የመልሶ ማጥቃት እና በቆሙ ኳሶች በንግድ ባንክ ሜዳ የሚደርሱት ወልዋሎዎች የመጀመርያ ሙከራቸውን በ37ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጎልነት ቀይረውታል። በተደራጀ የቡድን ስራ ወደ አደጋው ገጠና በመድረስ ዳዋ የሰጠውን ሳምሶን ጥላሁን በጥሩ ሁኔታ ከፍ አድርጎ ከተከላካ ይ ጀርባ የላከለትን የንግድ ባንኩ ተከላካይ ካሌብ ኳሱን ማራቅ ሳይችል በመቅረቱ ያገኘውን ዳዋ ሁቴሳ ግብጠባቂው ፍሬው ባጠበበት አቅጣጫ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ በአጋማሹ መጠናቀቂያ ተጨማሪ 46ኛው ደቂቃ ላይ ወልዋሎዎች ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዳዋ ሁቴሳ ከራሳቸው ሜዳ ያስጀመረውን ፉሀድ አዚዝ በድጋሚ ለዳዋ ሰጥቶት በፍጥነት እየገፋ ሄዶ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን እንደምንም በእግሩ አድኖበት ጨዋታው ወደ ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከሁለተኛው አጋማሽ አንስቶ ፍፁም የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከሁለቱ ኮሪደሮች ወደ ውስጥ በሚጣል ኳስ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት ንግድ ባንኮች ገና 60ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ ሰንዝረዋል። ኪቲካ ጅማ ከቀኝ መስመር ተጫዋች በመቀነስ ሳጥን ውስጥ በመግባት የመታውን ግብ ጠባቂው አሎሩንለኬ እንደምንም የመልሰውን ተከላካዮቹ ወደ ውጭ አውጥተዋል።
በሌላኛው የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የሊጉ ሻምፒዮን የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን የወንዶች ቡድንን ለማመረታታት በስታዲየሙ ከተገኙ በኋላ በ65ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎል አስቆጥረዋል። ከቀኝ መስመር ኪቲካ አፈትልኮ በመግባት የጣለውን በወልዋሎዎች ተከላካይ ሲመለስ ሳይመን ደገፍ አድርጎ የሰጠውን ተቀይሮ የገባው አብዱልከሪም መሐመድ በግሩም ሁኔታ መሬት ለመሬት በመምታት ጎል አድርጎታል።
እንደወሰዱት ብልጫ ተጨማሪ ጎል እንደሚያስቆጥሩ እንቅስቃሴያቸው የሚያሳየው ንግድ ባንኮች መሪ የሆኑበትን ሁለተኛ ጎል 75ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ከግራ መስመር አዲስ ግደይ ለበዛብህ ካቲሴ ሰጥቶት በዛብህ በተረከዝ ያሾለከለትን አዲስ ግደይ በሚታወቅበት መንገድ ኳሱን አዙሮ በቋሚው ቀኝ መረብ ላይ በማሳረፍ ግሩም ጎል አስቆጥሯል።
በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች መምራት ከጀመሩ በኋላ ወደ ኋላ ያፈገፈጉት ንግድ ባንኮች በወልዋሎዎች ጫና ውስጥ የገቡ ሲሆን በ87ኛው ደቂቃ ላይ ፉሃድ አዚዝ ከሞከረው አደገኛ ሙከራ በኋላ በተጨማሪ ደቂቃ የዕለቱ ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ ፊሺካ እየተጠበቀ ባለበት ቅፅበት በ97ኛው ደቂቃ ላይ በቡድን ስራ የተቀበለውን ኢሞሮ ማናፍ ቡድኑን ከሽንፈት የየታደገች የአቻነት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።