ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ድል አሳክቷል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ድል አሳክቷል

ቡናማዎቹ በኮንኮኒ ሃፊዝ ብቸኛ ግብ የጦና ንቦችን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ሁለት ከድል የተመለሱ ክለቦችን ያገናኘው የ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከ ወላይታ ድቻ አገናኝቷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሀዲያን 1-0 ከረቱበት አሰላለፍ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን በተመሳሳይ ወላይታ ድቻዎች አርባምንጭ ላይ ድል ከተቀዳጁበት አሰላለፍ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን አብነት ደምሴ እና ጸጋዬ ብርሃኑን በማስወጣት በምትካቸው ፍጹም ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰን አስገብተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተቀራራቢ የሆነ የኳስ ቁጥጥር እና እንቅስቃሴን ባስመለከተን ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል በመመስረት የመሃሉ የሜዳ ክፍል ላይ ብልጫ በመውሰድ መጫወት የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ወላይታ ድቻዎች ከመስመር በሚነሱ እና ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች የማጥቃት ዒላማቸው በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። በመጠነኛ ፉክክር በጀመረው ጨዋታ ቡናማዎቹ አጥቂያቸውን በጉዳት አጥተዋል። ከድቻ ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ ጋር የተጋጨው አንተነህ ተፈራ  እጁ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ለተሻለ ሕክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

በወላይታ ድቻ በኩል ከካርሎስ የርቀት ኳስ ሙከራ እና በቡናዎች ከኮንኮኒ የግንባር ኳስ ሙከራዎች በኋላ 23ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅጉን ለግብ የቀረበን ዕድል አባክነዋል። ከቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ሆኖ ኮንኮኒ ሃፍዝ ያቀበለውን ኳስ ከግቡ መስመር በአንድ እርምጃ ያክል ርቀት የነበረው በፍቃዱ አለማየሁ ያለምንም ግብ ጠባቂ እና ተጫዋች ነፃ ሁኖ ያገኘውን ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። ያንን የተመለሰ ኳስ በድጋሚ ያገኘው ኮንኮኒ ሃፍዝ ወደ ግብ ቢመታው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ይዞበታል። እነዚህ ሙከራዎች ለኢትዮጵያ ቡናዎች እጅጉን አስቆጪ አጋጣሚ ነበሩ።

የማጥቃት በትራቸውን በተጋጣሚ ቡድን ላይ በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያ አስቆጪ ሙከራቸውን ካደረጉ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ድጋሚ ግብ ማግኘት የሚችሉበትን ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በግራ መስመር በኩል ያገኙትን የቅጣት ምት ዲቫይን ዋቹኩዋ በቀጥታ መትቶ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰ ሲሆን በድጋሚ ያንኑ ኳስ ለግቡ በቅርብ ርቀት ላይ ሁኖ  ያገኘው ራምኬል ጀምስ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም የግቡ አግዳሚ በድጋሚ መልሶባቸዋል ይህም ዕድል ከነርሱ ጋር እንዳልነበረች ያሳየ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሁለቱም ቡድኖች በኳስ እንቅስቃሴው ረገድ ተመጣጣኝ የሆነ ጨዋታን ያስመለከቱን ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የድካማቸውን ፍሬ ያገኙበትን ግብ የአጋማሹ ጅማሬ ላይ ማስቆጠር ችለዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ዲቫይን ዋቹኩዋ በግራ መስመር የተጋጣሚ ተጫዋቾችን አታሎ በማለፍ ያሻማውን ኳስ ቁመተ ለግላጋው አጥቂ ኮንኮኒ ሃፊዝ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡናማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

የግቡ መቆጠር መነቃቃትን የፈጠረባቸው ወላይታ ድቻዎች በተደጋጋሚ ወደ ቡናዎች የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን 67ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው እንደምንም ብሎ ጨርፎ በግቡ አግዳሚ በኩል አስወጥቶቷል። በድጋሚ ያገኙትን ኳስ ናትናኤል ናሴሮ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ዳንላንድ ኢብራሂም ድንቅ በሆነ ችሎታ ጨርፎ በድጋሚ ወደ ውጭ አስወጥቶታል።

71ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች አማኑኤል አድማሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ዲቫይን ዋቹኩዋ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ጎል ከመሆን አግዶታል።

ይህንንም ተከትሎ በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኮንኮኒ ሃፊዝ ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።