አርባምንጭ ከተማ የተለያዩ አዳዲስ ውሳኔዎችን አስተላልፈ

አርባምንጭ ከተማ የተለያዩ አዳዲስ ውሳኔዎችን አስተላልፈ

የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከወቅታዊ የቡድኑ ውጤት ጋር በተያያዘ አዳዲስ ውሳኔዎችን እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሹመት ፈፅሟል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሁለት ጊዜያትን ያክል በመውረድ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ የቻለው አርባምንጭ ከተማ ባደገበት የ2017 የሊጉ የውድድር ጉዞው ካደረጋቸው 29 ጨዋታዎች 35 ነጥቦችን በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። በአሁኑ ሰዓት በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ በሚገኘው የሊጉ መርሀግብር ከሰባቱ በአንዱ ብቻ ድል የቀናው እና በተከታታይ ነጥቦችን እየጣለ የሚገኘው ክለቡ የቦርድ አባላት ለሁሉም የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ወደ አርባምንጭ ከተማ በመጥራት ካወያየ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ቡድኑን በቡድን መሪነት እና ቴክኒክ ሀላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው አንጋፋው የቀድሞው የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ተጫዋች የነበረውን ደጉ ደበበን ከቦታው በማንሳት ክለቡን ላለፉት ሁለት ዓመት ከግማሽ በስራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ አስጨናቂ ዳዊትን በስራ በቡድን መሪነት ሲሾም የቀድሞው የሀዋሳ እና ትራንስ ተጫዋች የነበረውን ረዳት አሰልጣኙ ገረሱ ሸመናን በማሰናበት በቦታው በመምህርነት ሙያ የሚሰሩት እና በአርባምንጭ ከተማ ወጣት ቡድን በተለይ ከ15 ዓመት በታች ላይ የሰሩትን አሰልጣኝ ገረመው ተበጀን ረዳት አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ሳይንስ መምህርነት እየሰሩ የነበሩት አሰገድ ከተማ በበኩላቸው ክለቡን በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ቦታ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ከአራት ዓመታት በፊት ክለቡን በስራ አስኪያጅነት የመሩት አቶ ዳዊት ኃይለማርያም በአንፃሩ ወደ ቀደመው የስራ አስኪያጅነት ቦታ ላይ የተመለሱ ሲሆን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ በረከት ደሙ ደግሞ በሦስት ጨዋታዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ቀጣይነታቸውን የሚወስን እንደሆነም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።