ነገ በታሪካቸው ለ51ኛ ጊዜ የሚገናኙ እና በጨዋታዎቹ በድምር 124 ግቦችን ያስቆጠሩ ቡድኖች የሚፋለሙበት ጨዋታ ለሐይቆቹ ከስጋት ቀጠናሙ ለመራቅ ለፈረሰኞቹ ደግሞ በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ለመደላደል ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።
በሁለተኛው ዙር የሚታይ ለውጥ ያመጣው ሀዋሳ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ያደረገውን ጉዞ አሳክቶ ከቀጠናው በአራት ነጥቦች ርቀት ላይ ተቀምጧል።
በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አስር ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት የቀመሰው ቡድኑ በተለይም ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ አስራ ሁለቱን ባሳካባቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት አድናቆት የሚያስችረው ነው። በውድድር ዓመቱ ወሳኝ ወቅት ላይ በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙ ክለቦች በተለየ በድሎች የታጀበ ተከታታይነት ያለው ጥሩ ብቃት ያሳየው ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ለመደላደል እና ከስጋት ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ግን አሁንም በያዘው የድል መንገድ መዝለቅ ግድ ይለዋል።
በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ላይ በሦስቱ ግቡን ያላስደፈረው እና በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ የመከላከል ጥንካሬውን ይዞ መዝለቁ ከተጠባቂው ጨዋታ አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ ሊያደርገው ቢችልም በመጨረሻው ጨዋታ ተጋጣሚን በሙሉ ኃይሉ እንዲያጠቃ ከጋበዘ ያፈገፈገ አቀራረብ ላይ ግን ውስን ለውጦች ማድረግ ሳይኖርበት አይቀርም። ከመጨረሻው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት የድሕረ ጨዋታ ቆይታ ከጨዋታ ይልቅ ለውጤቱ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የጠቆሙት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በነገው ዕለትም በተለመደው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እንደሚቀርቡ የሚጠበቅ ሲሆን በጨዋታ መጠናቀቅያ ደቂቃዎች ከሚገጥማቸው ጫና ለመላቀቅ ግን የግብ ማስቆጠር አቅማቸው ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ከረዷቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች በኃላ በመጨረሻው ጨዋታ በአዳማ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዳግም ወደ ድል መንገድ በመመለስ የሽቅብ ጉዟቸው ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በአርባ ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ በመጨረሻው መርሐግብር ሽንፈት ቢያስተናግዱም በጨዋታው የነበራቸው ብቃት ግን ብዙ አወንታዊ ጎኖች የነበሩበት ነው። ቡድኑ በሁለቱም አጋማሾች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ዕድሎችን በመፍጠር ተሽሎ ቢታይም በግብ ፊት የነበረው አፈፃፀም ግን ከጨዋታው ነጥብ ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል። ይህንን ተከትሎ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ጨዋታ ቀያሪ ዕድሎች የማባከን አባዜ መቅረፍ ከፈረሰኞቹ የሚጠበቅ ቀዳሚ ስራ ነው። ባላቸው አጨዋወት እና ከተጋጣሚያቸው አቀራረብ አንፃር በነገው ጨዋታ ፈረሰኞቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የሚይዙበት ዕድል የሰፋ ነው፤ ሆኖም ተጋጣሚያቸው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ያላስደፈረ የመከላከል ውቅር ያለው ቡድን እንደመሆኑ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይሆንም። የሚገኙትን ዕድሎች መጠቀምም ከቡድኑ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለተጋጣሚያቸው የመልሶ ማጥቃት ጥቃት ልዩ ዝግጅት ማድረግም ሌላው የሚጠብቃቸው የቤት ስራ ነው።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላቶች ለነገው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ እና ሄኖክ ዮሐንስ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ሀዋሳ ከተማ ገብተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች 50 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ ሀዋሳ ከተማ 8 ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪዎቹ 13 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ፈረሰኞቹ 86፣ ሐይቆቹ 38 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)