ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ የከተማውን ቆይታ በድል ዘግቷል

ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ የከተማውን ቆይታ በድል ዘግቷል

ሀይቆቹ 2-1 በሆነ ውጤት ፈረሰኞቹን በማሸነፍ ተከታታይ ሶስተኛ ድላቸውን በማሳካት ከተማቸውን ተሰናብተዋል።


በ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ምሽት 12 ሲል የጀመረው ጨዋታ ባለሜዳውን ሐዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አገናኝቷል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ያኔ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በተቃራኒው በአዳማ ከተማ የ1-0 ሽንፈትን ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተጫወቱበት አሰላለፍ ላይ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብጠባቂውን ባህሩ ነጋሽ ፣ ሄኖክ ዩሐንስ እና አብዱልሃፊዝ ቶፊቅን በማሳረፍ በምትካቸው ተመስገን ዩሐንስ፣ አብርሃም ጌታቸው እና ሀብታሙ ጉልላትን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ያለፈውን ጨዋታ ከአሸናፊነት እንደመመለሳቸው መጠን ያገኙትን ድል በማስጠበቅ ከወራጅነት ስሜት ለመላቀቅ ወደ ሜዳ ሲገቡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃሩ በአዳማ ከተማ ያጡትን ሶስት ነጥብ በዚህ ጨዋታ አስመልሰው ደረጃቸውን ወደ ላይ ከፍ ለማድረግ ይህንን ጨዋታ ትኩረት ሰጥተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ቀዝቀዝ ብሎ በተካሄደው የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን 25 ያክል ደቂቃዎች ሳቢ እና ለተመልካች ማራኪ ያልነበሩ ደቂቃዎችን ያስመለከተን ሲሆን በሁለቱም ቡድን በኩል ደካማ የሆነ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጭ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል።

28ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለግብ የቀረበ አስቆጪ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ፍፁም ጥላሁን ወደ ቀኝ በኩል ያሾለከለትን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ከግብጠባቂ ጋር የተገናኘ ቢሆንም ግን ኳሱን ሳይጠቀምበት የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጭ ወጥቷል ይህም ለፈረሰኞቹ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ 2 ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሐዋሳ ከተማዎች ጥሩ የሚባል ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን ቢንያም በላይ ከፍ አድርጎ ያቀበለውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ሳጥን ውስጥ አግኝቶ የሞከረውን ኳስ በተከላካዮች እና በግብጠባቂው ተጋድሎ ግብ ከመሆን ታድገውታል። ጨዋታው ሙሉውን አጋማሽ የተቀዛቀዘ ጨዋታን ያስመለከተን ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ብልጫን ወስደው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግተው ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ደካማ እንቅስቃሴን አስመልክተውናል።ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የተመለሱት ሀዋሳ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ማይክል ኦቱሉ እና አቤነዘር ዩሐንስን በማስገባት ወደ ሜዳ መግባት የቻሉ ሲሆን የሜዳውን የመሀል ክፍል መቆጣጠር ችለዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ በሜዳ ላይ የሚገኙ ደጋፊዎችን ደስተኛ ማድረግ የቻለ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ያገኙትን የማዕዘን ምት ዓሊ ሱሌይማን ያሻማ ሲሆን የተሻማውንም ኳስ እስራኤል እሸቱ በግንባር ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ለክለቡ መሪ መሆን የቻለበትን እንዲሁም በግሉ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚያግዛቸውን ግብ ለማግኘት ደጋግመው ጫና በመፍጠር መጫወት የቻሉ ሲሆን በአማኑኤል ኤርቦ ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ነገርግን በግብጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ጥረት ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል።

በጨዋታው መካከል ላይ በትንሹ መቀዛቀዝ ታይቶባቸው የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች 2ኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። 73ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ያቀበለውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ድንቅ የሆነ ግብን በማስቆጠር ክለቡን በሁለት ግብ ብልጫ መሪ ማድረግ ችሏል።

80ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አማኑኤል ኤርቦ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው መቆጣጠር ተስኖት የመለሰውን ኳስ ቢንያም ፍቅሬ ወደ ግብነት በመቀየር የግብ መጠኑን ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ችሏል።


ይህንንም ተከትሎ ሀዋሳ ከተማዎች 2-1 በማሸነፍ ተከታታይ ሶስተኛ ድላቸውን በማስመዝገብ ደረጃቸውን ወደ 10 ከፍ ማድረግ ችለዋል።