ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወደ ሜዳ የሚቀርቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እና በሀዋሳ  ቆይታቸው በሰባት የጨዋታ ሳምንታት ውስጥ ከወራጅነት ስጋት ወደ 4ኛ ደረጃነት የተመነደጉት ሲዳማ ቡናዎች የሚፋለሙት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።

በአርባ ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነገው ዕለት ድል ማድረግ ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ የሚሉበት ዕድል ይሰጣቸዋል።

ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ከረዷዋቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል ያባከኑት ፈረሰኞቹ ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ለመሻገር ወይንም ባሉበት አማካይ ቀጠና ለመደላደል ዳግም ወደ ድል መንገድ መመለስ ግድ ይላቸዋል። ፈረሰኞቹ ባለፉት አምስት መርሐ-ግብሮች በወራጅ ቀጠናው ዙርያ የሚገኙ ወልዋሎ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ቢገጥሙም የጠበቃቸው ፈተና ግን ቀድሞ ከተገመተው በላይ ነበር። ቡድኑ ከተጠቀሱት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥቦች ዘጠኙን ማሳካት ቢችልም ከተጋጣሚዎቹ ወቅታዊ ብቃት አንፃር ግን ከዚህም በላይ ማስመዝገብ ይገባው እንደነበር ይታመናል።

በሀዋሳ የስምንት የጨዋታ ሳምንታት ቆይታ ላይ በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ ወጥ የሆነ ብቃት ማሳየት ያልቻሉት ፈረሰኞቹ መጠኑ ይለያይ እንጂ በሁለተኛው ዙር ያደረጓቸው አብዛኞቹ ጨዋታ ተመሳሳይ የአፈፃፀም ድክመት የተስተዋለባቸው ናቸው። ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ ወጣ ገባ በሚል ብቃቱ ቢዘልቅም እንዲሁም ጉልህ የወጥነት ችግር ቢኖርበትም በጨዋታዎቹ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የነበረው ብቃት ግን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም። ሆኖም ጨዋታ ቀያሬ ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ድክመቱ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። የተሻለ የመጀመርያ አጋማሽ አሳልፎ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ ጨምሮ ቀድመው በተከናወኑ መርሐ-ግብሮች የተስተዋለውም ይህ ነው። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ማድረግ ከሚገባቸው ለውጦች በተጨማሪ የመከላከል አደረጃጀቱን ማሻሻል ሌላው የሚጠብቃቸው የቤት ስራ ነው። በተለይም በግብ ጠባቂዎቹ ላይ የሚስተዋለው የትኩረት እና የቦታ አያያዝ ችግር መቀረፍ የሚገባው ነው። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ባህሩ ነጋሽ እና ተመስገን ዮሐንስን አፈራርቆ ቢጠቀምም በሁለቱም ጨዋታዎች የተጠቀሱት ድክመቶች ተስተውለዋል።የነገው ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና ደግሞ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረና በጥሩ ብቃት የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ
የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ መሆኑ አይቀሪ ነው።

በአርባ ሦስት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እና በቅርብ ሳምንታት የውድድር ዓመት ጉዟቸውን ያቃኑት ሲዳማ ቡናዎች በሀዋሳ ከተማ ውጤታማ ጊዜ ካሳለፉ ክለቦች ይጠቀሳሉ።

በሀዋሳ ከተማ የመጀመርያ ጨዋታቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ በተከናወኑ ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ሲዳማ ቡናዎች በደጋፊያቸው ፊት መጫወታቸውን ተከትሎ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም አሟጠው በመጠቀም በሰንጠረዡ ወገብ ተቀምጠዋል።በ23ኛው ሳምንት ከወራጅ ቀጠናው በስድስት ነጥቦች ርቀው 12ኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች አምስት ድሎች እና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ  በጨዋታዎቹ ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አንድ ነጥቦች አስራ ሰባቱን ማሳካታቸውን ተከትሎ ከወራጅነት ስጋት ወደ 4ኛ ደረጃነት ተመንድገዋል።
ይህንን ተከትሎ በሀዋሳ የነበራቸው ውጤታማ ጉዞ በአዳማ መድገም ከአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ቡድን የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም ቡድኑ ከሽንፈት በራቀባቸው ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ መረቡን አስከብሮ የወጣው የተከላካይ መስመር እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ በያዙት ውጤታማነት መዝለቅ ይኖርባቸዋል።

በፈረሰኞቹ በኩል ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ እና ሄኖክ ዮሐንስ ከህመማቸው አገግመው ለነገው ጨዋታ ዝግጂ ሲሆን አጥቂው ተገኑ ተሾመ ግን በጉዳት የማይኖር ይሆናል። ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ሲዳማ ቡናዎች በነገው ጨዋተ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 29 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው በአንፃሩ ሲዳማ ቡና 2 ጊዜ አሸንፏል። 9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 39 ሲዳማ ቡና ደግሞ 12 ጎሎችን አስመዝግበዋል።