ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሽመክት ጉግሳ መጨረሻ ደቂቃ ብቸኛ ግብ መቻልን በማሸነፍ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ስንቅ የሆናቸውን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
መቻሎች በ34ኛው ጨዋታ ሳምንት በውድድር ዓመቱ ሻምፒዮኖች 2ለ0 ሲረቱ ይዘው ከገቡት ከመጀመሪያ ቋሚ አሰላለፍ የአራት ተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ዳዊት ማሞ፣ ነስረዲን ሀይሉ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና በረከት ደስታን አሳርፈው ዮዳዬ ዳዊት፣ ዳግም ወንድሙ፣ አቤል ነጋሽ እና ኮሊን ኮፊ ኩጆን ተክተው ሲገቢ አስቀድሞ በቋሚ ስብስብ ውስጥ ገብቶ የነበረው ኮሊን ኮፊ በማሟሟቅ ላይ እያለ በደረሰበት ጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆኖ ዳንኤል ዳርጌ እሱን ተክቶ መግባት ችሏል፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ 1ለ0 ሽንፈት ሲያስተናግዱ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው፤ አብዱላዚዝ አማን፣ ሄኖክ ገብረህይወት፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና ፍቃዱ አለሙን አሳርፈው በምትካቸው አበባየሁ ዮሐንስ፣ ኢዮብ ገብረማርያም፣ አሸናፊ ጥሩነህ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን ይዘው ገብተዋል።
ሁለት ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው ተጠባቂው የመቻል እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የሚደረስ ፍላጎቶች አሳይተው በማራኪ ፉክክር በትንሽ ንክኪ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየጣሉ ግብ ለማግኘት ጥረዋል። የመጀመሪያውን ሙከራ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ማድረግ የቻሉ ሲሆን መቻሎች ኳስ መስርተው ሊወጡ ሲሞክሩ አቤል ሀብታሙ ኳስ ቀምቶ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ ያደረገው ሙከራ ከግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ተመጣጣኝ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ መቻሎች መጀመሪያ አከባቢ የአጥቅቶ መጫወት ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ ወደ ማጥቃቱ የገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሌላኛውን አደገኛ ሙከራ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ላይ በተሰራ ጥፋት በተሰጣቸው ቅጣት ምት በአበባየሁ ዮሐንስ አማካኝነት አድርገው ለጥቂት ይውጣባቸው እንጂ ለግብ የቀረበ ሁለተኛው ሙከራ ይታወሳል። ጫናዎችን አጠናክረው የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች ጨዋታው 14ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሽመክት ጉግሳ ለአቤል ሀብታሙ አመቻችቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢያገናኘውም ሁለቱም ኳሱን ሳይደርሱበት ቀርተው የተሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አግኝቶ ወደ ግብ ለመምታት ሲዘጋጅ ዓለምብርሃን ይግዛው ሳይጠበቅ በግሩም ሁኔታ ከእግሩ ስር ኳስ አስወጥቶበታል።
በጨዋታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ሳጥን እየገቡ በግብ ቀዳሚ ለመሆን ሲጣጣሩ ብንመለከትም የመቻሉ በኃይሉ ግርማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ያሬድ የማነህ ከሳጥን ውጪ ሆነው አድርገው ዒላማቸውን ካልጠበቁ ሙከራዎች ውጭ በሁለቱም በኩል እድል የመፍጠሩ ነገር እየተቀዛቀዛ ሲመጣ አስተውለናል። አጋማሹ መቻሎች ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ተቸግረው የዋሉበት ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጋጣሚውን ቡድን ግብ ክልል በመድረስ ረገድ ብልጫ ቢወስዱም ይዘው የሚገቡትን እድሎች ጥድፊያ በተሞላበት እንቅስቃሴ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስመለክቱን ጨዋታው ቀጥሎ 37ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ እጅጉን ለግብ የቀረበ ሙከራ በኢዮብ ገብረማርያም አማካኝነት አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ በቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኢዮብ ገብረማርያም በድንቅ ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግብ አግዳሚ እጅግ በጣም ተጠግቶ ወጥቶበታል።
በግብ ማግባት ሙከራ አኳያ እጅግ ደካማ የነበሩት መቻሎች አጋማሹ መገባደጃ ላይ የተሻለ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ 41ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ሽመልስ በቀለ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ዓለምብርሃን ይግዛው ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ያመከነው እድል በአጋማሹ ግብ ለመሆን የቀረበ እድል ውጪ ሌላ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።
ያሉበት ደረጃ አስጊ ከመሆኑ አንፃር ነጥብ ይዘው ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በተደጋጋሚ ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ ጥቃት ሲሰነዝሩ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እጅግ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን አግኝተው ባለመረጋጋት አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ ሲቀሩ አስተውለናል፤ በተለይም በአጋማሹ መገባደጃ ላይ በጨዋታው ካደረጓቸው ሙከራዎች የላቀውን ያለቀ ኳስ አግኝተው ሳይጠቀሙ የቀረቡት አስቆጪው አጋጣሚ ሲታወስ አቤል ሀብታሙ ከመስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ኢላማውን ያልጠበቀ ኳስ ወደ መትቶ ሲያባክነው በዛ ቅፅበት ግብ ጠባቂው ጥፋት ሰርቶብናል ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል የሚል ቅሬታ አቅርበው የነበረ ቢሆንም የእለቱ ዳኞ ጨዋታውን በመልስ ምት አስጀምረውታል። አጋማሹም ግብ ሳያስመለክተን ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ተሻሽለው የቀረቡት መቻሎች ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት ሲጠጉ የተመለከትን ሲሆን 51ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ግሩም ሀጎስ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም በግቡ አናት ለጥቂት ባይወጣበት ከመልበሻ ክፍል መልስ ግብ አስቆጥረው ቀዳሚ ለመሆን የቀረቡበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሁለተኛውን አጋማሽ ተቀዛቅዘው ቀጥለዋል ቢሆንም ግን በ56ኛው ደቂቃ ላይ ጥቅ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው አቤል ሀብታሙ ከመሃል ሜዳ እየገፋ ይዘው የገባውን ኳስ የማቀበል እድል ቢኖረውም ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ግብ የመታውን ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይቆጣጠረው እንጂ አስቆጪው አጋጣሚ ነበር።
የተጫዋች ቅያሪ አድርገው በጥሩ ጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ሳጥን መግባት የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ65ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ እድል አግኝተው ውጤታማ ሳይሆን ይቅር እንጂ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል የገቡበት የአንድ ለአንድ ቅብብል ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል።
በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ሁለቱም ቡድኖች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቀጠለው በዚህ ጨዋታ መቻሎች እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ፈጥረው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፣ 67ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ በግራ መስመር እየገፋ ይዞ ገብቶ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ አቤል ነጋሽ ግብ ጠባቂውን አልፎ ያገኘውን ኳስ በማይታመን ሁኔታ ባልጠተበቁ መልኩ ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርጎ ያመከነው አጋጣሚ በጨዋታው እጅግ ለማመን የሚከብድ አስቆጪው ወርቃማ እድል ተጠቃሽ ነበር።
በሚቆራርጡ ኳሶች ግለቱ ቀንሶ እየተደረገ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ሲያመራ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻም መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ያሬድ የማነ ለናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያቃበለውን ኳስ እየገፋ ሳጥን ይዞት ገብቶ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ተመቻችቶ ሲጠባብቅ የነበረው ሽመክት ጉግሳ ኳስና መረብ አገናኝቷል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ለተጨማሪ ግብ ወደ ፊት የደረሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 89ኛው ደቂቃ ላይ አበበየሁ ዮሐንስ እና ሽመክት ጉግሳ ባደረጉት ቅብብል ሽመክት ጉግሳ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ በድንቅ ቅልጥፍና ኳሱን ባያወጣባቸው ሁለተኛ ግብ አስቆጥረው በእፎይታ ጨዋታውን እንዲጨርሱ ሊያደርጋቸው የቀረበ አጋጣሚ ይጠቀስ እንጂ ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኝ ሶስት ነጥብ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አስገኝቶ መቋጫውን አድርጓል።