የሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ 0ለ0 ተቋጭቷል።
ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋው የ1ለ1 የአቻ ውጤት ጨዋታ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ቅያሪዎን ሲያደርጉ ጊት ጋትኩትን በዮሴፍ ዮሐንስ ፣ ሬድዋን ናስርን በፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ሲተኩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል በፈፀሙት አርባምንጮች በኩል ደግሞ በአራቱ ላይ ለውጦች ሲደረጉ ፀጋዬ አበራ ፣ በርናንድ ኦቼንግ ፣ ቻርለስ ሪቫኑ እና አህዋብ ብሪያንን ፣ በአሸናፊ ፊዳ ፣ ካሌብ በየነ ፣ መሪሁን መስቀሌ እና አሸናፊ ተገኝ ተተክተዋል።
ከረጅም ዓመታት በኋላ ሁለተኛ የሊግ ጨዋታውን ረፋዱን ያስተናገደው የወንጂ ስታዲየም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን ማስተዋልን ብንችልበትም በሙከራዎች ግን ብዙም ያልደመቀበት ነበር። በአርባምንጭ በኩል በፍቅር ግዛው ከሳጥን ውጪ መቶ የግብ ዘቡ መስፍን ሙዜ የመለሰበት እና ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ይገዙ ቦጋለ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ያገኛትን ኳስ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ሳጥኑ ጠርዝ በግብ ዘቡ ፋሪስ ዕላዊ ያመከነበት አጋጣሚ ከላይ በተጠቀሱት ደቂቃዎች ውስጥ የተመለከትናቸው ስልነት ያልነበራቸው ሙከራዎች ሆነዋል። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ተጭኖ በመጫወት ከሀያ አምስት ደቂቃዎች በኋላ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማዎች በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ያገኙትን መልካም አጋጣሚ ይገዙ ቦጋለ ቢያገኛትም ግብ ጠባቂው ፋሪስ ዕላዊ አምክኖበታል።
በመልሶ ማጥቃት አህመድ ሁሴንን ባማከለ ማጥቃት የሚጫወቱት አዞዎቹ በመረጡት የጨዋታ መንገድ የመጨረሻው ሜዳ ላይ ሲደርሱ በተደጋጋሚ መረጋጋት ስላልነበራቸው የሚያጠቁበት መንገድ በድግግሞሽ ሲቋረጥባቸው ተስተውሏል። እንደነበራቸው ብልጫ ጥራት ባለው ሙከራ ጥረታቸውን ማጎምራት ያልቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ጭማሪ 45+2 ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ካደረጋት እና ፋሪስ ዕላዊ ካዳናት ሙከራ መልስ አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ሲዳማ ቡና ፈጣን አጀማመርን በማድረግ ሀብታሙ ታደሠ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ተጫዋቾችን በመቀነስ ያደረጋት ሙከራን ፋሪስ በያዘበት አጋጣሚ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀጠለ እንቅስቃሴ ጨዋታው የበዛበት ነበር። የተጫዋቾች ቅያሪን በማድረግ በአዲስ ጉልበት ጨዋታቸውን ማድረግ የቀጠሉት ቡድኖቹ ሲዳማ ቡና በአንድ ሁለት ቅብብል ጨዋታውን በመቆጣጠር የተሻሉ መሆን የቻሉበት አርባምንጮች ደግሞ በረጃጅም ኳሶች የተጫወቱበት ቢሆንም በግብ አጋጣሚዎችን ግን አሁንም ብዙ መድመች ሳይችል ቀርቷል።
74ኛው ደቂቃ በአርባምንጭ በኩል አሸናፊ ተገኝ በመስፍን ሙዜ የወጣበት እንዲሁም በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች የአርባምንጭን መከላከል ማስከፈቱ የከበዳቸው ሲዳማ ቡናዎች ከሳጥን ውጪ መስፍን ታፈሠ ሞክሮ ፋሪስ ዕላዊ ያዳበት እና ጨዋታው ሊጠናቀቅ 89ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ በኩል የተገኘውን የቅጣት ምት በዛብህ መለዮ በቀጥታ መቶ የግቡ የላይኛው ብረትን የገጨችበት በጨዋታው የታየች ጥራት የታከለባት ሙከራ ሆና በመጨረሻም ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል።