አህጉራዊ የክለቦች የውድድር የጊዜ ሰሌዳ ታወቀ

አህጉራዊ የክለቦች የውድድር የጊዜ ሰሌዳ ታወቀ

የ2025/26 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድሮች የሚካሄዱበት ቀናት ይፋ ሆኗል።

የአህጉራችን ከፍተኞቹ የክለቦች የውድድር መድረክ የሆኑት የቻምፒየንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ካፕ መድረኮች ሀገሮች እንዳላቸው ኮታ እንዲሁም እንደሚከተሉት ደንብ የሊግ እና የጥሎ ማለፍ የበላዮችን የሚያሳትፍ ሲሆን ሀገራችንም ኢትዮጵያ መድንን እና ሲዳማ ቡናን በሁለቱ ታላላቅ ውድድሮች እንደምታሳትፍ ቀድሞ መረጋገጡ ይታወሳል። ከሌሎቹ ሀገራት በመጠኑም ቢሆን የተለየ የውስጥ የውድድር የጊዜ መርሐ-ግብር (Calendar) የምትከተለው ሀገራችን ኢትዮጵያ ክለቦቿ በአህጉራዊ ጨዋታዎች ላይ እምብዛም ገፍተው ባይጓዙም ከመደበኛው የሊግ ጨዋታዎች ጋር በትንሹ የሚቃረኑ ቀናት ሲገጥሙ ማስተዋል የተለመደ ነው።

ከካፍ እየወጡ ባሉ መረጃዎች መሰረት የካፍ የክለቦች የውስጥ ውድድሮች የሚጀምሩበት ጊዜ ሲታወቅ የመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከመስከረም 9-11 እንዲሁም የመልሱ ከመስከረም 16-18 ድረስ እንደሚደረጉ ታውቋል። የሁለተኛ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ደግሞ ከጥቅምት 7-9 እንዲሁም የመልሱ ደግሞ ከጥቅምት 14-26 ድረስ እንደሚደረጉ ተገልጿል። ከቅድመ ማጣሪያዎቹ በኋላም ከኅዳር 12 ጀምሮ የምድብ ጨዋታዎች የሚከናወኑ ሲሆን በወርሃ መጋቢት የግማሽ ፍፃሜ በወርሃ ሚያዚያ የሩብ ፍፃሜ እንዲሁም በወርሃ ግንቦት የፍፃሜ ጨዋታ እንደሚከናወኑ የወጣው የውድድሮቹ የመርሐ-ግብር ሰሌዳ ያሳያል።

የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ከወትሮ ጊዜ ወደፊት የተገፉበት ምክንያት ከሳምንታት በኋላ በሚጀምረው የቻን ውድድር እንደሆነም ተመላክቷል።

በተያያዘ ዜና ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25 ድረስ የመጀመሪያ ዙር የቡድን አባላት ምዝገባ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።