ዓለም-አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት የሲዳማ ቡና ይግባኝ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ውሳኔ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፋይናንስ መመሪያ ጥሰት በመፈፀማቸው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ቅጣት የተላለፈባቸውን ክለቦች እና ተጫዋቾችን ጉዳይ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ እና ከዓለም ዓቀፍ ስፖርታዊ አሰራር ውጪ እንዲታይ በማድረግ “የተጫዋቾችን ዕግድ አስነስተናል” በሚል ከፌዴሬሽኑ ፈቃድ ውጪ ተጫዋቾቹን ሲያሰልፉ የቆዩ ክለቦች እነዚህን ያልተገቡ ተጫዋቾችን ባሰለፉባቸው ጨዋታዎች በሙሉ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ጉዳዩን ወደ ዓለምአቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት (CAS) በመውሰድ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን የይግባኝ ሂደቱም በቁጥር “CAS 2025/A/11595 Sidama Bunna Football Club Vs Ethiopian Football Federation” ተመዝግቦ እየታየ ቆይቷል።
ከቀናት በፊት ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ የክስ ሂደቱ በሚታይበት ወቅት የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ያቀረበውን ጥያቄ የዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) የይግባኝ ግልግል ክፍል ተመልክቶ ውድቅ ማድረጉን ፌዴሬሽኑ ማሳወቁ ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት (CAS) ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ያስመዘገበው የይግባኝ ክስ በፍርድቤቱ መመሪያ (CAS Code) መሠረት የቅደም-ተከተል ሂደቱን ያልተከተለ እና የይግባኝ ፍሬ ሃሳቡ በሰነድ መልክ ያልቀረበበት በመሆኑ የተቀመጠው ቀነ-ገደብ ካለፈ በኋላ ክለቡ በማስተካከያነት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የይግባኝ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ በመወሰን የኬዝ ፋይሉን መዝጋቱን በፍርድቤቱ የይግባኝ ግልግል ክፍል ምክትል ፕሬዘዳንት ፊርማ በወጣ የትዕዛዝ ደብዳቤ አሳውቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዚህን የፍርድ ሂደት ዝርዝር ጉዳዮች አስመልክቶ በቀጣይ ሳምንት በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የተሟላ የህግ ሰነድ ዶሴውን ለሚዲያ ይፋ የሚያደርግ እና በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያዎችን የሚሰጥ መሆኑን እናሳውቃለን።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲዳማ ቡና ስፖርታዊ ግጭቶች የሚፈቱበትን የፊፋ እና የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መመሪያዎች በመከተል ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) መውሰዱ የሚበረታታ ትክክለኛ አሰራር መሆኑን ይገልፃል።”