አዞዎቹ በሊጉ ከአሰልጣኛቸው ጋር ይቀጥላሉ

አዞዎቹ በሊጉ ከአሰልጣኛቸው ጋር ይቀጥላሉ

በተጠናቀቀው ዓመት ሁለት መልክ የነበረውን የውድድር ጉዞን ያስመለከተን አርባምንጭ ከተማ ከአሰልጣኝ በረከት ደሙ ጋር ለመቀጠል ስምምነትን ፈፅመዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለሁለት ጊዜያቶች ያህል ለመውረድ የተገደደው እና በቀድሞው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አሰልጣኝ በረከት ደሙ አማካኝነት በተጠናቀቀው ዓመት በሊጉ በመካፈል ሁለት ገፅታ የነበራቸውን የውድድር መልኮችን ያሳለፈው አርባምንጭ ከተማ የፋይናንስ ህጉን በተላለፉ ክለቦች ላይ ከተወሰነው ውሳኔ በኋላ በተሻሻለው የደረጃ ሰንጠረዥ ምክንያት በመጨረሻም አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ከቡድኑ ጋር የውል ዘመናቸውን ያጠናቀቁት አሰልጣኝ በረከት ደሙ ቀጣዩንም ዓመት በክለቡ እንደሚቆዩ ሁለቱም አካላት ስምምነትን ማድረግ እንደቻሉ እንዲሁም ወደ ስራ መግባታቸውን ዝግጅት ክፍላችን ለማወቅ ችላለች።

ከአዞዎቹ የተከላካይ አማካይ ተጫዋችነት በኋላ የክለቡን ወጣት ቡድን በማሰልጠን አሰልጣኝነት የጀመሩት አሠልጣኝ በረከት በ2015 በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይ አርባምንጭን በፕሪምየር ሊጉ ቢረከቡም ክለቡ ባስመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት የተነሳ ከሊጉ ለመውረድ መገደዱ ይታወቃል። ከቡድኑ ጋር ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርደው በማሰልጠን በተጠናቀቀው ዓመት በሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ ዕርከን ላይ እንዲሳተፍም ማድረግ የቻሉት አሰልጣኙ ከአንድ ዓመት የሊጉ ቆይታ በኋላ ቀጣዩንም ዓመት በክለቡ እንደሚቆዩ ለማረጋገጥ ችለናል።

በአሁኑ ሰዓት በክለቡ ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም ንግግር የጀመረው ክለቡ አንጋፋውን የቀድሞው ተከላካይ ደጉ ደበበን ወደ ቡድኑ ዳግም የቀላቀለ ሲሆን የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውርም በቅርቡ እንደሚፈፅሙም ጭምር ሰምተናል።