በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የጦና ንቦቹን የሚገጥመው ክለብ ሲዳሰስ…?
በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ቢያስተናግዱም በፍትሕ አካላት ውሳኔ መሰረት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፋቸውን ያረጋገጡት ወላይታ ድቻዎች ከትናንት በስቲያ ተጋጣሚያቸውን አውቀዋል። በሊብያ ዋንጫ አል አህሊ ቤንጋዚን የረታው አል ኢቲሃድም በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የኢትዮጵያውን ተወካይ የሚገጥም ክለብ ሆኗል።
አል-ኢቲሃድ ስፖርት ክለብ ማን ነው?
አል-ኢቲሃድ ስፖርት ክለብ በሊብያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በባብ ቤን ጋሺየር በተባለ አከባቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከተመሰረተ 81 ዓመታት ያስቆጠረ አንጋፋ ክለብ ነው። የሊቢያን ፕሪምየር ሊግ 18 ጊዜ፣ የሊቢያን ዋንጫ 7 ጊዜ፣ የሊቢያ ሱፐር ካፕ 11 ጊዜ እንዲሁም በ2001 የካፍ አሸናፊዎች ዋንጫ ያሸነፈው ክለቡ በሊብያ ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸው ክለቦች ቀዳሚው ሲሆን የሀገሪቱን ሊግ በማሸነፍም ቀዳሚው ነው። ክለቡ ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ ከአስደናቂው የሦስት ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ በኋላ የተጫወተበት ክለብም ነው።
በካፍ ውድድሮች ያላቸው ታሪክ እና ከኢትዮጵያ ክለቦች ያላቸው የግንኙነት ታሪክ?
አል ኢቲሃድ ከዚህ ቀደም በ27 አጋጣሚዎች በካፍ ውድድሮችን የተሳተፈ ሲሆን 15 ጊዜያት በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ፤ 11 ጊዜያት በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ እንዲሁም በአንድ አጋጣሚ በ2004 ወደ ካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ በተጠቃለለው ‘African Cup Winners Cup’ መሳተፍ ችለዋል። በ2001 በአንጋፋው ውድድር ‘CAF Cup Winners Cups’ ያሸነፉበት እንዲሁም በ2007 በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ በ2010 ደግሞ በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ላይ ግማሽ ፍፃሜ የደረሱበት ደግሞ በክለቡ ታሪክ ምርጡ ውጤታቸው ነው።
አል ኢቲሃድ በ1985 ዓ.ም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ማጣርያ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገናኝቶ ነበር። ትሪፖሊ ላይ በተካሄደው የመጀመርያው ጨዋታ አል ኢቲሃድ ሦስት ለባዶ ሲያሸንፍ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተካሄደው የመልስ ጨዋታ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለአንድ ረቷል፤ በድምር ውጤትም አል ኢቲሃድ አራት ለሁለት በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር አልፏል።
የክለቡ አሰልጣኝ?
የወቅቱ የአል ኢቲሃድ አሰልጣኝ በአህጉረ አፍሪካ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ሁዋን ካርሎስ ጋሪዶ ናቸው። ጋሪዶ በአፍሪካ እግር ኳስ ልምድ ያላቸው ስፔናዊ አሰልጣኝ ሲሆኑ በታሕሳስ 30 2017 ቡድኑን ለአጭር ጊዜ ያሰለጠነውን ኦሳማ አል ሃማዲን በመተካት ቡድኑን ለሰባተኛ ጊዜ የሊብያ ዋንጫ አሸናፊ ማድረግ ችለዋል። ከዚህ ቀደም በቪያርያል፣ ርያል ቤቲስ፣ ክለብ ብሩዥ፣ አል አህሊ እንዲሁም ራጃ ካዛብላንካ ጨምሮ በርከት ያሉ ክለቦችን ያሰለጠኑት አሰልጣኙ በተለይም በአፍሪካ ውድድሮች ትልቅ ልምድ አላቸው።
የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች?
በዘንድሮ የውድድር ዓመት በአል-ኢቲሃድ ትሪፖሊ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ በርካታ ቁልፍ ተጫዋቾች ቢኖሩም የፊት መስመር ተጫዋቹ አሕመድ አል ሀራም የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው።
በዋና አጥቂነት እንዲሁም በመስመር ተጫዋችነት የሚሰለፈው ይህ የ29 ዓመት ተጫዋች በካፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ልምድ ያለውና ከሀያ በላይ አህጉራዊ ውድድሮች ማድረግ የቻለ ነው። ካህራባ፣ ቱሚሳንግ ኦሬቦኔ እንዲሁም በቅርቡ ካይዘር ቺፍስን ለቆ ክለቡን የተቀላቀለው ታያዮኔ ዲትልሆክዌም የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
ክለቡ የሚጫወትበት ስታዲየም?
አል ኢትሃድ የሜዳውን ጨዋታ ከመሀል ትሪፖሊ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ትሪፖሊ ስታዲየም ያደርጋል። 45,000 ደጋፊዎች የመያዝ አቅም ያለው ይህ ስቴድየም አል-አህሊ ትሪፖሊ እና የከነአን ማርክነህ የቀድሞ ቡድን አል መዲና በጋራ ይጠቀሙበታል። ክለቡ አል ማላብ አል ባላዲ የተሰኘ 5,000 ደጋፊዎች የመያዝ አቅም ያለው በማዕከላዊ ትሪፖሊ የሚገኝ ስታዲየም ያለው ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ሜዳው በማሰልጠኛ ማዕከልነት እያገለገለ ነው።