ስሑል ሽረ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ከጫፍ ደርሷል

ስሑል ሽረ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ከጫፍ ደርሷል

ስሑል ሽረዎች በቅርብ ቀናት አዲስ አሰልጣኝ ይሾማሉ።

ለዓመታት ከእግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ ውጭ ሆነው ከቆዩ በኋላ ባለፈው የውድድር ዓመት ወደ ሀገራዊ ውድድር ተመልሰው የውድድር ዓመቱን በ 27 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ስሑል ሽረዎች የቀድሞ አሰልጣኛቸው ዳንኤን ፀሐዬን በዋና አሰልጣኝነት ለመቅጠር ከጫፍ ደርሰዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ አሰልጣኙ እና የስሑል ሽረ አመራሮች ከዚህ ቀደም ተገናኝተው በጉዳዩ ዙርያ የመከሩ ሲሆን አሁን ደግሞ ደግሞ ሁለቱም አካላት ከስምምነት ለመድረስ ከጫፍ ደርሰዋል። በ2016 የመቻል ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ባለፈው የውድድር ዓመት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የአስር ወራት ቆይታ የነበረው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በ2010 ስሑል ሽረን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳልፎ በ2011 አጋማሽ ላይ ከቡድኑ ጋር በስምምነት መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዳግም ቡድኑን ለማሰልጠን ከጫፍ ደርሷል።


ዳንኤል ፀሀዬ ከ1987 እስከ 1999 በዘለቀው የእግር ኳስ ሂወቱ አስራ አንድ ዓመታት በጉና ንግድና አዳማ ከተማ እንዲሁም በሦስት የዕድሜ ዕርከኖች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወቃል። ወደ ስልጠናው ዓለም ከገባ በኋላም በደደቢት ወጣትና ዋና ቡድን፣ ስሑል ሽረ፣ አክሱም ከተማ፣ መቻል፣ መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ስር በምክትል አሰልጣኝነት ሰርቷል።