በክረምቱ የዝውውር መስኮት ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርመው የነባሮችን ውል ያደሱት አዲስ አዳጊዎቹ ሸገር ከተማዎች አሁን ደግሞ የአምስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል።
ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያሳለፈውና ከሁለት የተለያዩ ክለቦች የሊጉን ዋንጫ ያነሳው የቀድሞ የጅማ አባጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ፣ ሁለተኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ደግሞ የፊት መስመር ተጫዋቹ አንተነህ ተፈራ ሲሆን በክልል ክለቦች ሻምፒዮን ውድድር በሻኪሶ ከተማ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ቡና በማምራት ያለፉትን ሦስት ዓመታት በቡናማዎቹ ቤት ቆይታ ካደረገ በኋላ ማረፍያው ሸገር ከተማ ሆኗል።
ሦስተኛው ፈራሚ ደግሞ አድናን ረሻድ ነው፤ ባለፈው የውድድር ዓመት በአዳማ ከተማ መለያ ስምንት ግቦች ያስቆጠረው ይህ ወጣት ተጫዋች በአምቦ ፕሮጀክት ከተገኘ በኋላ በጅማ አባ ጅፋር እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአዳማ ከተማ ቆይታ አድርጎ አሁን መዳረሻው ሸገር ከተማ ሆኗል።
አራተኛው ፈራሚ ደግሞ ተከላካዩ ፍቅሩ አለማየሁ ሲሆን ከለገጣፎ ፕሮጀክት ተገኝቶ እስከ ዋናው ቡድን ከተጫወተ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአዳማ ከተማ በግሉ ጥሩ የውድድር ዓመታት አሳልፎ ሸገር ከተማን ተቀላቅሏል።
አምስተኛ ፈራሚው ወጣቱ የግራ መስመር ተከላካይ አቤል አየለ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኋላ በሰንዳፋ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ እንዲሁም ባለፈው የውድድር ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታ ያደረገ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊው ቡድን ፌርማውን አኑሯል።