የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኤግዚቢሽን ጨዋታውን ባደረገ ማግስት ለሙከራ አሜሪካ ከቀሩት ተጫዋቾች ውስጥ እነማን ተመርጠዋል የሚለውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ባሳለፍነው ሐምሌ 26 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ ተጉዞ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር የኤግዚቢሽን ጨዋታ አድርጎ 3ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። ሆኖም ከዲሲ ዩናይትድ የመጡ መልማዮች በአራት የዋልያዎቹ ተጫዋቾች ማለትም በከነዓን ማርክነህ ፣ ቢኒያም በላይ ፣ ሐብታሙ ተከስተ እና ራምኬል ጀምስ ላይ ዐይናቸውን በማሳረፍ የሙከራ እድል መስጠታቸው ይታወቃል።
ተጫዋቾቹ የሙከራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በዝግጅት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀላቅለዋል። ሆኖም ለተጫዋቾች የሙከራ ጊዜ ውጤታቸው በፌዴሬሽኑ ኢሜይል በኩል ይፋ እንደሚደረግ የተነገራቸው ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ከታማኝ ምንጮቿ ባገኘችው መረጃ ከሆነ ከነዓን ማርክነህ እና ቢኒያም በላይ ዲሲ ዩናይትድን እንዲቀላቀሉ ክለቡ ለጊዜው ፍላጎት ያሳየ መሆኑን ያረጋገጥን ሲሆን የሐብታሙ ተከስተ እና ራምኬል ጀምስ ጉዳይ ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ታማኙ ምንጫችን አረጋግጦልናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖር አዳዲስ ነገሮች ካሉ በቀጣይ የምንመለስበት መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን ።