ሽረ ምድረገነት በዝውውር መስኮቱ የመጀመሪያ ፈራሚዎቹን አግኝቷል።
ቀደም ብሎ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐየን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሮ እስካሁን ድረስ በዝውውሩ ተሳትፎ ሳያደርግ የቆየው ሽረ ምድረገነት አሁን የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አገባዷል።
ቀዳሚው ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው ተጫዋች በተጠናቀቀው ውድድር ዓመት በፋሲል ከነማ ቆይታ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ተካልኝ ደጀኔ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በፋሲል ከነማ ቆይታ የነበረው ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዐፄዎቹ ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ማረፍያው ሽረ ምድረ ገነት ሆኗል።
ሁለተኛው ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው ተጫዋች ደግሞ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሲዳማ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ ቆይታ የነበረው ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እንዲሁም ከ2014 ጀምሮ በሲዳማ ቡና ቆይታ እንደነበረው የሚታወስ ሲሆን ባለፈው ዓመት አጋማሽ ከአራት ዓመታት የሲዳማ ቡና ቆይታ በኋላ ከቡድኑ ተለያይቶ ወደ መቐለ 70 እንደርታ አምርቶ የስድስት ወራት ቆይታ ካደረገ በኋላ አሁን ደግሞ ወደ ሽረ ምድረገነት ለማምራት ፊርማውን አኑሯል።