👉 “ዕድሎችን አልተጠቀምንም እንጂ ጥሩ ጨዋታ አድርገናል።”
👉 “የዝግጅት ጊዜ ማነሱ በመጠኑም ቢሆን ጎድቶናል።”
👉 “ከሜዳ ውጭ ለሚገጥሙን ፈተናወች ከወዲሁ እንዘጋጃለን።”
በካፍ ኮንፌደሬሽን ኢትዮጵያን ወክለው በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከሊቢያ አቻቸው አል ኢትሃድ ትሪፖሊ ጋር ጨዋታቸውን ያደረጉት የጦና ንቦች 0-0 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ስለ ጨዋታው እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ተጋጣሚያችን በዚህ መድረክ ትልቅ ልምድ ያለው ሲሆን እስከ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻለ ጠንካራ ቡድን ነው። እኛ በተቃራኒ ቡድኑን እንደ አዲስ እያዋቀርን ነው ያለነው ከዛ አንጻር አሪፍ ጨዋታ ነው ማለት እንችላለን ያው ያገኘናቸውን እድሎች መጠቀም ባንችልም።”
“በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ አዳዲስ ልጆችን ይዘን ነው ወደ ዝግጅት የገባነው ይሄ በመጠኑም ቢሆን ጎድቶናል።”
“ተጋጣሚያችን ከባድ እና ጠንካራ ቡድን ነው በሜዳቸው ለሚገጥሙን ፈተናወች ከወዲሁ እንዘጋጃለን።”