በመቐለ 70 እንደርታ የዳግመኛ ምስረታ ታሪክ የመጀመርያው አሰልጣኝ የሆነው ፀጋዘአብ ባሕረጥበብ እና የዘጠናዎቹ ድንቅ አጥቂ መድሃኔ ታደሰ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ተመልሰዋል።
በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ ካደረጉ ክለቦች የሚጠቀሱት እና በክረምቱ የዝውውር መስኮት አስር ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምተው የአራት ነባር ተጫዋቾች ውል ለማራዘም ከስምምነት የደረሱት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ፊታቸውን የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ወደ ማዋቀር በማዞር ሁለት ባለሞያዎችን ቀጥረዋል። ቡድኑን የተቀላቀሉ ደግሞ ፀጋዘአብ ባሕረጥበብ እና መድሃኔ ታደሰ ናቸው።
አሰልጣኝ ፀጋዘአብ ባሕረጥበብ በመቐለ 70 እንደርታ ዳግመኛ የምስረታ ታሪክ (1998) የመጀመርያው አሰልጣኝ ሲሆን ከዚህ ቀደም በትግራይ ውሀ ስራዎች፣ ደደቢት እንዲሁም በ2017 በመቐለ 70 እንደርታ የታዳጊዎች መልማይ ሆኖ ሲሰራ ከቆየ በኋላ በ2011 በደደቢት አብሮት ከሰራው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ጋር ዳግም አብሮ ለመስራት በምክትል አሰልጣኝነት ቡድኑን ተቀላቅሏል።
ሁለተኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ደግሞ በቅርቡ በካፍ ፋስት ትራክ ‘B’ ዲፕሎማውን የያዘው የሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው የዘጠናዎቹ ድንቅ አጥቂ መድሃኔ ታደሰ ነው። በተጫዋችነት ሕይወቱ በትራንስ ኢትዮጵያ፣ መቻል፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ዳሽን ቢራ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም ደደቢት ከተጫወተ በኋላ ጫማውን የሰቀለው የቀድሞ አጥቂ አሁን ደግሞ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሆኖ ለመስራት ከስምምነት ደርሷል።