በ2026 በፖላንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ የኬንያ አቻቸውን ያስተናገዱት ትናንሾቹ ሉሲዎች ጨዋታቸውን 1ለ1 አጠናቀዋል።
በ2026 በፖላንድ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ 9፡00 ሲል በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ሲደረግ ጨዋታው በዝናባማ የዓየር ሁኔታ እና ውሃ በቋጠረው የአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጅማሮውን ሲያደርግ ኬንያዎች በ27ኛ ሴኮንድ ጎል አስቆጥረዋል። በሌላ ተጫዋች ተሞክሮ ግብ ጠባቂዋ አበባ አጄቦ መቆጣጠር ያልቻለችውን ኳስ ኤልዛቤት ሚዴቫ ልዋንጉ መረብ ላይ አሳርፋዋለች።
ኬንያዎች ለመጫወት ምቹ ባልሆነበት ምክንያት በነበራቸው የአካል ብቃት ብልጫ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ ትናንሾቹ ሉሲዎች በአንጻሩ 16ኛ ደቂቃ ላይ በእሙሽ ዳንኤል አማካኝነት የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል።
ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ኢትዮጵያዊያን በማጥቃቱ እንቅስቃሴ መነቃቃት እያሳዩ ቢሄዱም የሜዳው ለጨዋታ ምቹ አለመሆን ፈተና ሲሆንባቸው ተስተውሏል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲመለስ 62ኛ ደቂቃ ላይ ኬንያዎች ተጨማሪ ያለቀለት የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል። በዚህም ዲያና ኦቾል ከ ኤምሊ ኮሙንቶ ጋር ተቀባብላ በወሰደችው ኳስ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ አበባ አጄቦ እንደምንም ጎል ከመሆን ታድጋዋለች።
ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን በቀጠሉት ኢትዮጵያዎች በኩል 68ኛ ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት ሙከራ ግሩም ሙከራ ብታደርግም በግብ ጠባቂዋ ተመልሶባታል።
ጨዋታው 67ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ እሙሽ ዳንኤል ከሳጥኑ ጠርዝ የመታችው ኳስ በግብ ጠባቂዋ እግሮች መሃል ሾልኮ የአቻነት ግብ ሲሆን በዚሁ በተነቃቁት ትናንሾቹ በኩል ራሷ እሙሽ ዳንኤል በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ጠንካራ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ ከሽፎባታል።
ከዕረፍት መልስ ከፍተኛ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ኢትዮጵያውያን 89ኛ ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ዙፋን ደፈርሻ ከረጅም ርቀት የመታችው ኳስ የግቡን ብረት ገጭቶ ተመልሷል። ከደቂቃዎች በኋላም ዳግማዊት ሰለሞን ከእሙሽ ዳንኤል በተቀበለችው ኳስ ያደረገችው ሙከራ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባታል። ይህም እጅግ አስቆጪ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።
* የመልሱ ጨዋታ ከሳምንት በኋላ መስከረም 18 ናይሮቢ ላይ ይካሄዳል።