አዳማ ከተማዎች ቡድናቸውን ማጠናከር ተያይዘውታል

አዳማ ከተማዎች ቡድናቸውን ማጠናከር ተያይዘውታል

አዳማ ከተማዎች ስድስት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምተዋል።

ሀይደር ሸረፋን፣ አቡበከር ሳኒ፣ አሕመድ ሑሴን፣ አላዛር ማርቆስ፣ ብዙአየሁ ሰይፉ፣ ኢዮብ ማቲያስ፣ ዓብዱልከሪም መሐመድን ለማስፈረም ተስማምተው የነባር ተጫዋቾች ውል ለማራዘም ከስምምነት የደረሱት አዳማ ከተማዎች አሁን ደግሞ ሰባት ተጫዋቾች ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።


በ2017 የውድድር ዓመት በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ ያደረገው እና ከዚህ ቀደም በባህርዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ መጫወት የቻለው የመሀል ተከላካዩ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል። ሌላው ባለፈው ዓመት በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ የነበረው እና በውድድር ዓመቱ በ31 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2666′ ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው የቀድሞ የደደቢት፣ ሽረ ምድረገነት፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ የመስመር ተከላካይ መድሐኔ ብርሀኔም ሌላው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማ ተጫዋች ነው።

ሦስተኛው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ደግሞ
ሁለገቡ ሳሙኤል ዮሐንስ ነው። በ2017 የውድድር ዓመት በሀድያ ሆሳዕናና ወልዋሎ መለያ ዓመቱን ያሳለፈው ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድኑ እስከ ዋናው ቡድን በመጫወት እግር ኳስ ጀምሮ በአማራ ውሃ ስራ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልዋሎ፣ ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮጵያ መድን እና በሀድያ ሆሳዕና መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ አዳማ ከተማ ለማምራት ከስምምነት ደርሷል።

አራተኛው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው እንደ ሳሙኤል ዮሐንስ በወልዋሎ ቆይታ ያደረገው አማካዩ ሚራጅ ሽፋ ነው።የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ውጤት የሆነው ይህ ተጫዋች ለፈረሰኞቹ ታዳጊና ዋና ቡድን እንዲሁም ለሸገር ከተማ መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ አዳማ ከተማን ለመቀላቀል ተስማምቷል።


ወደ ቡድኑ ለማምራት የተስማማው አምስተኛው ተጫዋች ደግሞ በ2017 የውድድር ዓመት በወልዋሎ እና ሽረምድረ ገነት ቆይታ ያደረገው አላዛር ሽመልስ ነው። ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ለገጣፎ ለገዳዲና ሸገር ከተማ መጫወት የቻለው የመስመር ተጫዋቹ አሁን ደግሞ በዝውውሮች ራሱን በማጠናከር ላይ ወደ ሚገኘው አዳማ ከተማ ለማምራት ከስምምነት ደርሷል። አዳማ ከተማን ለመቀላቀል የተስማማው ስድስተኛው ተጫዋች ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ አዲስ አበባ ከተማ ቆይታ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ሔኖክ ካሳሁን ነው።

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ መሪነት የተጠቀሱትን ተጫዋቾች ጨምረው በከተማቸው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ልምምዳቸውን ከጀመሩ አምስት ቀናቶች አስቆጥረዋል።