መቐለ 70 እንደርታ ሁለት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምቷል

መቐለ 70 እንደርታ ሁለት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምቷል

ምዓም አናብስት ከቀናት በፊት ለማስፈረም ከተስማማሙት ተጫዋች ጋር ሲለያዩ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።


በመጀመርያው ሳምንት ሽረ ምድረ ገነትን የሚገጥሙት እና ቀደም ብለው ስንታየሁ መንግስቱን ለማስፈረም የተስማሙት መቐለ 70 እንደርታዎች ከቀናት በፊት አፍቅሮት ሰለሞንን ለማስፈረም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ስብስቡን ተቀላቅሎ ልምምድ ከጀመረ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ከክለቡ ጋር መቀጠል አልቻለም። በዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ለማስፈረም እንዲሁም የነባሮችን ውል ለማራዘም የተስማምሙት ምዓም አናብስት አሁን ደግሞ ሁለገቡ ዮሐንስ ዓፈራ እና ግብ ጠባቂው ሐድሽ በርሐ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ሶሎዳ ዓድዋ ቆይታ የነበረውና በግራ መስመር ተከላካይነት እንዲሁም በአማካይነት መጫወት የሚችለው ዮሐንስ ዓፈራ የመቐለ 70 እንደርታ ሁለተኛ ቡድን ፍሬ ሲሆን ከዚ ቀደምም በቡራዩ ከተማ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ሶሎዳ ዓድዋ፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ በመቐለ 70 እንደርታ መለያ በክልል አቀፍ ውድድር ሲወዳደር የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ እናት ክለቡ ተመልሷል። ሌላው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ግብ ጠባቂው ሐድሽ በርኸ ከዚህ ቀደም በትግራይ ውሃ ስራዎች፣ ደደቢት እንዲሁም በ2016 በመቐለ 70 እንደርታ መጫወት የቻለ ተጫዋች ሲሆን አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል።