የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !
ኢትዮጵያ ቡና ከ ነገሌ አርሲ
ቡናማዎቹ እና ሰጎኖቹ የሚያደርጉት የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ 07፡00 ሲል ይጀምራል።
በአሰልጣኝ ዐቢይ ካሳሁን የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰባቸውን ሽንፈት የሚያካክስ ድል ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባሉ። በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጫወተው ቡድኑ በሸገር ደርቢ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የታየበት ክፍተት ጉልህ ነበር። ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣውን ግብ ጠባቂውን ዳንላድ ኢብራሂም አገልግሎት አያገኝም።
በአሰልጣኝ ቱሉ ደስታ የሚመሩት እና በመጀመርያው የጨዋታ ሳምንት ላይ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ባደረጉት የፕሪምየር ጨዋታ ከአዞዎቹ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ነገሌ አርሲዎች ኢትዮጵያ ቡናን በሚገጥሙበት ጨዋታ ላይ የመጀመርያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ጉልህ የሆኑ ዕድሎችን የመጠቀም ክፍተት የታየባቸው አዲስ አዳጊዎቹ በክለቡ ታሪክ የመጀመርያዋን የፕሪምየር ሊግ ግብ አስቆጣሪው ሀቢብ ከማል በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።
ሸገር ከተማ ከ አዳማ ከተማ
በክረምቱ የዝውውር መስኮት እንደ አዲስ የተገነቡ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ 10፡00 ሲል ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ሸገር ከተማዎች በመጀመሪያው ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያጋጠማቸውን የ1ለ0 ሽንፈት ቀልብሰው አጀማመራቸውን ለማሳመር የዛሬውን ድል አጥብቀው ይፈልጉታል። የታየበትን የመሃል ሜዳ ስፍራ ቁጥጥር ክፍተት ለመድፈን ከትናንት በስቲያ ናትናኤል ዘለቀን ያስፈረመው ቡድኑ ለዛሬው ጨዋታ በሙሉ ዝግጁነት እየተጠባበቀ ይገኛል።
በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እየተመሩ በመጀመሪያው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ጎል ሲለያዩ በተለይም በማጥቃት ሽግግሩ በኩል ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩት አዳማ ከተማዎች የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ፍለጋ ከሸገር ከተማ ጋር ይጫወታሉ። በጨዋታው ላይ አምበላቸውን ሐይደር ሸረፋን በሁለት ቢጫ ያጡት አዳማዎች ነቢል ኑሪ ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ሚራጅ ሰፋን በጉዳት የማያሰልፉ ሲሆን በልዩ ፍቃድ የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ የመሩት የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ለዛሬው ጨዋታጨሙሉ ለሙሉ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው የቡድኑ መልካም ዜና ነው።
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ፋሲል ከነማ
የሀዋሳ ምድብ የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በቢጫዎቹ እና በዐፄዎቹ መካከል 9፡00 ሲል ይጀምራል።
በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመሩት ወልዋሎዎች በመጀመሪያው ሳምንት ሲዳማ ቡናን 1ለ0 እየመሩ ዕረፍት ቢወጡም ከዕረፍት መልስ ባልተጠበቀ ሁኔታ 4ለ1 ተሸንፈዋል። ሆኖም ቡድኑ ከደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት ለማገገም የዛሬውን ጨዋታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። በዕለቱ ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣው ብሩክ እንዳለ በዛሬው ጨዋታ ላይ የማይሰለፍ ሲሆን የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ኮንኮኒ ሀፊዝ የወረቀት ሥራውን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ታውቋል። የዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ጆኤል ሙታክብዋ መሰለፍ ግን ዛሬ የሚታወቅ ይሆናል።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አድርገው ግብ ካስቆጠሩ በሁለት ደቂቃ ልዩነት በተቆጠረባቸው ጎል 1ለ1 መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን ከሕዳሴ ዋንጫ ጀምሮ እየታየባቸው የሚገኘውን የመከላከል ሽግግር ክፍተት መድፈን የዛሬ ጨዋታቸው ትኩረት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዐፄዎቹ በኩል ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ እና ሃብታሙ ተከስተ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ሲሆን ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀለው ያሬድ ብርሃኑ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ወላይታ ድቻ ከ ድሬዳዋ ከተማ
በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት የጦን ንቦች እና ብርቱካናማዎቹ ምሽት 12፡00 ሲል ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመሩ ከመቻል ጋር ያደረጉትን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ባስተናገዱት ግብ በሽንፈት ያጠናቀቁት የጦና ንቦቹ ከዚህ አስቆጪ ሽንፈት ለማገገም ዛሬ ከብርቱካናማዎቹ ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በድሬ ካፕ ቻምፒዮን ከሆኑ ማግስት በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 መሸነፋቸው ይታወሳል። ሆኖም ቡድኑ እንዳለፈው የውድድር ዓመት ጠንካራ አጀማመር ለማድረግ የዛሬውን ድል አጥብቆ እየፈለገ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። በብርቱካናማዎቹ በኩል ጀሚል ያዕቆብ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሲሆን ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።